ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገለጸ
ሀዋሳ ፤መጋቢት 09/2013 (ኢዜአ)፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተቀረፁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር የትምህርት ጥራትና አግባብነት ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም በተቋሙ የ10 ዓመት መሪ እቅድ ዙሪያ እየመከረ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ እንዳሉት፤ መድረኩ በትምህርት ሴክተሩ ለሚቀረፁት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂዎችና መሪ ዕቅዶች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ይበልጥ ዳብረው እንዲፀድቁ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን ለማሰባሰብ የተዘጋጀ ነው።
እስካሁን ስንመራበት የቆየው የትምህርት ሥርዓታችን በርካታ መቀረፍ የሚገባቸው ችግሮች አሉበት ያሉት ዶክተር አያኖ በተለይ የትምህርት ጥራት ፣ አግባብነትና ፍትሀዊነት ላይ ሰፊ ጉድለቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በተደራሽነት በኩል የተሻለ ቢሆንም ከሌሎች አቻ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በሀገር ደረጃ እየተቀረፁ ያሉት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እነዚህን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀመጡ መሆናቸውን አመልክተው ዩኒቨርሲቲው መሪ ዕቅድም ከዚህ ጋር አስተሳስሮ መቃኘቱን አስረድተዋል።
የተጠቀሱ ችግሮችን በማቃለልና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ በማድረግ ብቃት ያላቸው ምሩቃንን ለማፍራት ዩኒቨርስቲው እንደሚራ አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍስሀ ጌታቸው በበኩላቸው ሀገሪቱ ስትመራበት የቆየችው ፖሊሲና ስትራቴጂክ ገበያው የሚፈልገው የሰው ኃይል በማጥናት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ተጽዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን ተናግረዋል።
በተለይ የትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት ባለመሰራቱ ብቁና በራሳቸው ሥራ መፍጠር የሚችሉ ዜጎችን የማፍራቱ ጉዳይ አንገብጋቢ ችግር እንደሆነ አውሰተዋል።
20 ሚሊዮን የሚጠጉ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ባሉባት ኢትዮጵያ የትምህርት አካታችነትና ፍትሐዊነት ጉዳይም መዘንጋቱን ጠቅሰዋል።
የኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ለማረጋገጥ የተሟላም ባይሆን ጅምር ሥራዎች እንዳሉት ያመለከቱት ዶክተር ፍስሀ በተለይ የመምህራንን አቅም ለመገንባት ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።
ጥልቀት ባይኖረውም የገበያ ጥናትን መሠረት ባደረገ መልኩ አዳዲስ ፕሮግራሞችን ለመክፈት እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው እነዚህን በጎ ጅምሮች አጠናክሮ በማስቀጠል በሥነ-ልቦና የበቁና ስብዕናቸው የተሟላ ምሩቃንን ለማፍራት እንደሚተጋ አስታውቀዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ በኃይሉ እሸቱ ሀገሩን የሚወድና ለማሳደግ የሚተጋ ትውልድ ለማፍራት የተሟላና አካታች የትምህርት ፖሊሲ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ያለፍንበት የትምህርት ሥርዓት በዕውቀት ፣ ክህሎትና ሥነ-ምግባር ብቁ ያልሆኑ ምሩቃንን በተግባር ያየንበት ነው ያሉት አቶ በኃይሉ እየተቀረፀ ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችሉ የአሰራር ስልቶችን ይዞ የቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በሚያፈራቸወረ ምሩቃን ጥራትና ብቃት ላይ ያተኮረ፤ በተለይ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመግቢያና መውጫ ፈተና መስጠትን እንደ አንድ ስልት ማስቀመጡ የነበሩ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት አመቺ አቅጣጫ መሆኑን አስረድተዋል።
ገበያው የሚፈልገውን የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት እንዲቻል ስርዓተ ትምህርት ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሀገራዊ ተቋም ለመመስረት እንደ አቅጣጫ መቀመጡም ከትምህርት አግባብነት አኳያ ያሉ ሰፊ ክፍተቶችን ለመሸፈን የሚስችል ነው ብለዋል።
የተነደፉትን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ወደ ተግባር መቀየር ከተቻለ በዕውቀት ፣ ክህሎትና አመለካከት የበቁ ምሩቃንን ማፍራት እንደሚቻል ገልጸው ለዚህ እውን መሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የምክክር መድረኩ ከዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች የተውጣጡ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።