ቀጥታ፡

በምግብና መድኃኒት ዙሪያ የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

ደሴ፤ መጋቢት 9/2013 (ኢዜአ) በሰዎች ጤና ላይ እከል የሚፈጥሩ ምግብና መድኃኒት ዙሪያ የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ጥሪ አቀረበ፡፡

ባለስልጣኑ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መፍታት በሚቻልበት ዙሪያ ከባለድርሻ ጋር በደሴ ከተማ ተወያይቷል፡፡

በውይይት መድረኩ የባለስልጣኑ  ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄራን ገርባ እንደገለጹት በምግብና መድኃኒት ላይ የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራት የዜጎችን ህይወት እስከማሳጣት ያደርሳል፡፡

በተለይ የትና መቼ እንደተመረቱ፤ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው መቼ እንደሚያበቃ የማይታወቁ፤ መገለጫ የሌላቸው፤ ከባዕድ ቁሳቁስ ጋር እየተቀላቀሉ ገበያ ላይ የሚውሉ ምርቶች መበራከት አሳሳቢ ሆኗል ብለዋል።

ድርጊቱ ውስብስብ በመሆኑ ሁሉም የየድርሻውን በመወጣት በሰው ጤና ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በትብብር ለመከላከል ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ችግሮችን ለማቃለል ባለስልጣኑን በአዲስ በማደራጀት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው  ከሀገር ውጭ የሚገቡና በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ለህዝብ ጤና ደንታ በሌላቸው ግልሰቦች አሁንም ጨለማንና አሳቻ ሰዓት ተጠቅመው አደገኛ የምግብና የመድሃኒት ምርቶችን ለህብረተሰቡ የሚያሰራጩ መኖራቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

በቅንጅት ተከታትለው ለህግ እንዲቀርቡና በጥፋታቸው ልክ እንዲቀጡ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው ህብረተሰቡም በመጠቆምና በማጋለጥ የበኩሉን  እንዲወጣ አሳስበዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የምርት ደረጃና ጥራት ቁጥጥር ባለሙያ አቶ አስረስ አስናቀ በበኩላቸው በዘርፉ የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራትን ለማስቆም ፈታኝና አቅም የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

 ህገ ወጥ ደላሎችና ነጋዴዎች ባለሙያን በማስፈራራት ጭምር እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ ራሳችንን ለአደጋ አጋልጠን የምንይዛቸው እንኳ ተገቢውን ቅጣት እያገኙ አይደለም ብለዋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ጠንካራ ህብረት ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃለፊ ኮማንደር መሃመድ አበጋዝ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቅርቡም ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀለ ማር ሲሰሩና ሲያከፋፍሉ የተገኙ ግለሰቦችን ለህግ አቅርበው እንዲቀጡ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ምግብና መድኃኒት ከሰው ህይወት ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው የዜጎችን ህይወት ለመታደግ የድርሻዋን ለመወጣ ዝግጁ መሆኗን የተናገረችው ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት ዘቢባ አሊ ናት፡፡

በመድረኩ ከፌደራል፣ ክልል፣ ዞንና  ደሴ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ የጸጥታና የፍትህ አካላት፣ እንዲሁም የሐይማኖት አባቶች ፡የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም