የኢትዮጵያን የአንድነትና የመቻቻል ባህል ለመገንባት ቤተ እምነቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው - ምክትል ከንቲባ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የአንድነትና የመቻቻል ባህል ለመገንባት ቤተ እምነቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው - ምክትል ከንቲባ
አዲስ አበባ መጋቢት 9 /2013 ( ኢዜአ ) የኢትዮጵያን የአንድነትና የመቻቻል ባህል ለመገንባት ቤተ እምነቶች ከፍተኛ ሚና ያላቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት 36ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው እለት አካሂዷል።
በጉባኤው ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባዋ የኢትዮጵያን የአንድነትና የመቻቻል ባህል ለመገንባት ቤተ እምነቶች ከፍተኛ ሚና ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በአገሪቱ እየታየ ያለውን መከፋፈል በማውገዝ የአንድነትና የመቻቻልን ባህልን ለመገንባት ወሳኝ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
ህብረቱ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር ያለውን አንድነትና ህብረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዘዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ሰላም፣ አብሮነትና መቻቻል ቤተ እምነቶች የጎላ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከፊታችን ያለው አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅና አሳሳቢውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል ቤተ ዕምነቶች የሚጠበቅባቸውን ሊያደርጉ ይገባልም ነው ያሉት።
''በእምነትነና በዘር ልዩነት ውስጥ ሆነን ያለፍንባቸውን አመታት እያስታወስን መጋጨት ቁስልን በማከክ እንዲያገረሽ ያደርገዋል እንጂ አያድነውም በማለት እምነታችን እንደሚያስተምረን እርቅ ለማውረድ በይቅርታ መተላለፍ ዋነኛው መፍትሄ ነው'' ብለዋል።
የህብረቱ የቦርድ ሰብሳቢ ፓስተር ሰንበቶ ባሼ በበኩላቸው አገር የሚቀጥለው፣ ሰው ወጥቶ የሚገባው ተምሮ ለቁም ነገር የሚበቃው ሰላም ሲኖር በመሆኑ በተለይ ወጣቱ ለዚህ እውን መሆን መቆም አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት 36 ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።