አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የንግድና ዘርፍ ማህበራት ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የንግድና ዘርፍ ማህበራት ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ
መጋቢት 9/2013 (ኢዜአ) የኢፌዲሪ ቆንስል ጀኔራል መሪ አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የንግድና ዘርፍ ማህበራት ሊቀመንበር ሚስተር ሰሚር ናስ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ፤ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ትስስር በሚጠናከርበት ዙሪያ በባህሬን መወያየታቸው ተገልፇል።
አምባሳደር ጀማል በውይይታቸው በኢትዮጵያ ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
ሀገሪቱ እያካሄደች ካለው አጠቃላይ የሪፎርም ስራ አንዱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የተከፈቱ አዳዲስ መስኮችን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ በምግብ እራስን ከመቻል አንጻር አግሮ ፕሮሰሲንግና ማኑፋክቸሪንግ ላይ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎች፣ አምራች የሰው ሃይል ያለ መሆኑን አስረድተው፤ ባህሬናዊያን በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የእንስሳት ተዋጽኦ፣ ቡና ፣ አትክልትና ፍራፍሬና ሌሎች ምርቶችን ከኢትዮጵያ ወደ ባህሬን ማስገባት በሚቻልባቸውና በቱሪዝም ዘርፍ በሀገሪቱ በዩኒስኮ የተመዘገቡ ታላላቅ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ለቱሪስት ምቹ መሆናቸውን በማስገንዘብ ባህሬናዊያን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙና የቱሪዝም ምርጫቸው እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል አምባሳደር ጀማል በሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርን ለማሳደግና ለማጠናከር ከዚህ ቀደም በሁለቱ አገራት የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች መካከል ለመፈራረም የተደረገው የመግባቢያ ሰነድ ልውውጥ ወደ ፊርማ እንዲሸጋገር አበክረው አንደሚሰሩና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራውን በማጠናከር ግንኙነቱን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳለቸው ገልጸዋል።
የባህሬን የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ሰብሳቢ በበኩላቸው አምባሳደሩ ያደረጉላቸውን ማብራሪያ አድንቀው፤ ባህሬናዊያን ኢንቨስተሮችና ነጋዴዎች በኢትዮጵያ ባለው የኢንቨስትመንት እድሎች እንዲሳተፉ ለማድረግ አበክረው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡
የባህሬን ነጋዴዎች ከኢትዮጵያ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ የመሳሰሉ ምርቶችን ወደ ባህሬን እንዲያስገቡ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸው ተገልፇል።
በቀጣይም ከኢትዮጵያ አቻቸው የኢትዮጵያ የዘርፍና ሴክቶሪያል ማህበራት ምክር ቤት ጋር መገናኘት እንደሚፈልጉ፣ ሁለቱ ምክር ቤቶች የተለዋወጡትን መግባቢያ ሰነድ በቅርቡ መፈራረምና የቢዝነስ ለቢዝነስ ፎረም ማካሄድ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የቢዝነስ ልኡካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክና ያሉትን የኢንቨስትመንትና ንግድ እድሎች በማየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመወያየትት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ማለትም የንግድ፣ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ስራን ለማሳደግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ባህሬን የሚያደርገውን በረራ በድጋሚ እንዲጀመር ጠይቀዋል ተብሏል።
በአጠቃላይ በሁለቱም ኃላፊዎች በተነሱት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራትና ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በተጨማሪም ሁለቱ ምክር ቤቶች ከዚህ ቀደም የተለዋወጡትን መግባቢያ ሰነድ በቅርቡ በሚሲዮኑ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ በሚካሄደው ፕሮግራም ጎን ለጎን መፈራረም እንዲቻልና የቢዝነስ ለቢዝነስ ፎረም ማካሄድ እንዲቻል በውይይታቸው አንስተው መግባባት ላይ ተደርሷል።
በመጨረሻም አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የንግድና ዘርፍ ማህበራት ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአገሪቱ ያሉትን የኢንቨስትመንትና ንግድ እድሎች በስፋት በማብራራት እንዲሁም በውጭ ቀጥተኛ ኦንቨስትመነት ላይ በአገሪቱ ያሉ ህጎችና አሰራሮች፣ የተደረጉ ማሻሻያዎች የሚያተጉና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱን የሚያበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደር ባህሬናዊያንም ሆኑ በዚህ ያሉ ሁሉም ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲደርጉም ጥሪ ማቅረባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡