የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊና ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን ለሁሉም ተፎካካሪዎች እኩል እድል ሊሰጡ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊና ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን ለሁሉም ተፎካካሪዎች እኩል እድል ሊሰጡ ይገባል ተባለ
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊና ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል እድል ሊሰጡ እንደሚገባ ተጠቆመ። ጋዜጠኞችም ገለልተኛ ሆነው በመስራት ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተወጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል።
ስልጠናው በምርጫ አዘጋገብ ዙሪያ ባለሙያዎች መከተል ስለሚገባቸው ሥነ ምግባር በማሳወቅ አቅምን ለማሳደግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
በስልጠናው በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሥነ ምግባር ደንብ እና አተገባበር ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን የጋዜጠኞች መብትና ግዴታም ተዳሷል።
የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ጋዜጠኞች በቀጣዩ ምርጫ ዙሪያ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ በማቅረብ በኩል ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው።
ምርጫው ተአማኒና ሰላማዊ መሆን እንደሚገባው የገለጹት አቶ አማረ ለዚህ ደግሞ ትክክለኛና ለህዝቡ በቂ መረጃ እንዲደርስ ማድረግ የባለሙያው ግዴታ መሆኑን አክለዋል።
የአቅም ግንባታ ስልጠናውም ይህንን ዓላማ ለማሳካት መዘጋጀቱን ጠቁመው ተመሳሳይ ስልጠናዎች በሌሎች ክልሎች እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
የህግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ግርማ በምርጫ የሥነ ምግባር ደንብ እና አተገባበር ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም በተለይ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል እድል መስጠት እንዳለባቸው በደንቡ ላይ ተቀምጧል ብለዋል።
ፓርቲዎች በውይይትም ይሁን በክርክር ጊዜ እኩል ሽፋን እንዲያገኙ በደንቡ ላይ የተቀመጠውን መርህ በመከተል መተግበር ይገባል ብለዋል።
"በምርጫ አዘጋገብ የሚፈጠሩ ክፍተቶች ከግለሰብና ድርጅቶች ባለፈ በአገር ላይም አሉታዊ ጫና የሚፈጥር ነው" ያሉት ባለሙያው ዘገባዎች ጥንቃቄ የታከለባቸው እንዲሆኑም አመልክተዋል።
ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት ድምጽ የሚሰጥበትን ሚስጥራዊ ቦታ ቪዲዮ መቅረጽና ፎቶ ማንሳት የተከለከለ መሆኑን ገልጸው መራጮች ቃለ መጠይቅ መስጠት ካልፈለጉ ማስገደድ እንደማይቻልም አብራርተዋል።
ከዚህ ባለፈም የምርጫ ውጤት ሳይታወቅ ማንኛውም ፓርቲ አሸንፏል የሚል ዘገባ ማውጣት በደንቡ የተከለከለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የሚሰሩ ዘገባዎችም እውነት እና በማስረጃ የተደገፉ መሆን እንደሚገባቸው አቶ ሰለሞን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዘገባ ወቅት የአንድ ፓርቲ ምልክት ወይም አርማ የያዘ ቲሸርት መልበስ፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ምርጫውን በተመለከተ ምክር መለገስ፣ መራጮች ስለመረጡት ፓርቲ ወይም የግል ተወዳዳሪ ማንነት መጠየቅ እንደማይቻልም በደንቡ መካተቱን አስታውቀዋል።
"የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ምርጫውን በሚመለከት የወጡ ህጎችና ደንቦችን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው" ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ታምራት ሃይሉ ናቸው።
መገናኛ ብዙሃንም በስራቸው ያሉ ጋዜጠኞችን አቅም ለማሳደግ በስልጠናና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።