ቀጥታ፡

አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ አበረከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9/2013 (ኢዜአ) አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ አበረከተ፡፡

ባንኩ ድጋፍን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በዛሬው እለት አስረክቧል፡፡

የባንኩ የኦፕሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን አሰፋ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ባንኩ ድጋፉን የለገሰው ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ያለውን አጋርነት ለማሳየት ነው።

በመሆኑም በዛሬው እለት ለግድቡ ግንባታ አጋዥ የሚሆን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በስጦታ አበርክቷል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ባንኩ ላደረገው ድጋፍ በማመስገን አርአያነት ያለው ተግባር መፈፀሙንም ጠቅሰዋል።

የአንድነታችንና የሉዓላዊነታችን መገለጫ ለሆነው ህዳሴ ግድብ ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁም መላ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ከግድቡ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሩች ቢኖሩም በጋራ መቆምና መመከት ያስፈልጋል ብለዋል።

አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ከዚህ ቀደም ለኮቪድ 19 ወረርርሽኝ መከላከያ፣ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ማጠናከሪያ፣ ለገበታ ለአገርና ለሸገር ማስዋብ ፕሮጀክቶች ግንባታ 16 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም