ግብጽና ሱዳን በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን ሰላም በማወክ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል እየሰሩ ነው - የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽና ሱዳን በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን ሰላም በማወክ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል እየሰሩ ነው - የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9/2013 (ኢዜአ) ግብጽና ሱዳን በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን ሰላም በማወክ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል እየሰሩ በመሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመቆም ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲከታተሉ አመራሮቹ ጠይቀዋል።
አቶ የሺዋስ አሰፋ ከኢዜማ፣ ኢንጅነር ግደይ ዘርዓጺኦን ከትዴፓ እንዲሁም ዶክተር ያሬድ ተሾመ ከብልጽግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
የፖለቲካ አመራሮቹ በቆይታቸው ሁለቱ ሃገራት የኢትዮጵያን ሰላም በተለያዩ አጋጣሚዎች በማወክ የህዳሴው ግድብ ግንባታና ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አማካሪ ኢንጅነር ግደይ ዘርዓጺኦን እንዳሉት ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳታከናውን ሲሰሩ የነበሩ ሀገራት ዛሬም ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ በጋራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አገራቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያን ሰላም በማወክ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል እየሰሩ በመሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት እንዲፈጠርና ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ኢንጅነር ግደይ አብራርተዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በተጠናከረ መልኩ በጋራ በመቆም አንድነታቸውን በማስጠበቅና ሰላማቸውን በማረጋገጥ ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ያሬድ ተሾመ እንዳሉትም ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት በማከናወን የተያዘውን እቅድ ማሳካት የሀገሪቷን ሉዓላዊነትም ማስከበር ያስፈልጋል።
ለሁለተኛው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት ዕቅድ መሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የግድቡ ጉዳይ የኢትዮጵያን የጋራ ትልም፣ የጋራ ስኬትና የጋራ ግብ በመሆኑ ከፖለቲካ ልዩነት በመውጣት ለጋራ አጀንዳ በጋራ መቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት ዶክተር ያሬድ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው ግብጽና ሱዳን የህዝባቸውን ጥያቄ ላለመመለስ የህዳሴ ግድብን ግንባታ ለፖለቲካ ፍጆታቸው እያዋሉት መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱ አገራት ግድቡን የውስጥ ፖለቲካ ችግራቸው መፍትሄ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሃገራቱ በኢትዮጵያና በህዳሴ ግድቡ ውሃ ሙሌት ጉዳይ ከመግባት ተቆጥበው የራሳቸውን የቤት ስራ መስራት አለባቸውም ብለዋል፡፡
በግድቡ ግንባታ ጉዳይ ኢትዮጵያዊያን ያለልዩነት በጋራ መቆም አለባቸው ሲሉም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘው ዓመት 590 ሜትር ከፍታ ላይ የሚደርስ ሲሆን የ11 ተርባይኖችን ተከላ እንደሚከናወንም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በተያዘው ዓመት ክረምት ሁለተኛው ዙር 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚሞላና ሁለቱ ተርባይኖች ሃይል የማመንጨት የሙከራ ፍተሻ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።