በላስ ቬጋስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ላይ የሚደረገውን ያልተገባ ታልቃ ገብነት በመቃወም ሰልፍ አካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
በላስ ቬጋስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ላይ የሚደረገውን ያልተገባ ታልቃ ገብነት በመቃወም ሰልፍ አካሄዱ
መጋቢት 9 / 2013 (ኢዜአ) በላስ ቬጋስ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ባደረጉት ሰልፍ የህወሃት ቡድን በኢፌዲሪ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈፀም ያስከተለውን የሰላም ማደፍረስ እና የክህደት ወንጀል በማውገዝና በመቃወም ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ በሕወሃት ስርዓት ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ የዳያስፖራ ቡድኖች አባላት ግፊት በኢትዮጵያ ላይ በአንዳንድ የአሜሪካ የህግ አውጪ እና የህግ አስፈፃሚ አካላት የሚደረገውን ያልተገባ ዲፕሎማሲያዊ ጫናም ተቃውመዋል።
በላስ ቬጋስ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እና የላስ ቬጋስ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ንዑስ ቡድን አባላት ባስተባበሩት በዚህ ሰልፍ ላይ በርካታ የላስ ቬጋስ ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፎ አድርገዋል።
የዳያስፖራ አባላቱ ለአገራቸው እና ለመንግስት ያላቸውን ድጋፍ የገለፁ ሲሆን በዲፕሎማሲው ረገድ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ኢ-ፍትሃዊ ጫና በተደራጀ መንገድ ለመቋቋም ከመንግስት ጋር በመቀናጀት ለመታገል መወሰናቸውን አረጋግጠዋል።
ሰልፈኞቹ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያንፀባርቅ ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫ እና ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በሰልፍ ስነ-ስርዓቱ ላይ የጁንታው ቡድን እና ተባባሪዎቹ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀሙትን አሰቃቂ ወንጀሎች በማውገዝ፣ አሜሪካን ጨምሮ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን በጥንቃቄ በመመርመር ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጥ ጥሪ የሚያቀርቡ እና ሌሎችም ወቅታዊ መፈክሮችን አሰምተዋል።
በመጨረሻም ሰልፈኞቹ ጥያቄያቸውን በኔቫዳ ግዛት ተመራጭ ለሆኑ ሁለት ሴናተሮች እና አራት የኮንግሬስ አባላት በፅሁፍ ማቅረባቸውን የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።