ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሥነ-መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ከውጭ ሀገር ተማሪዎችን ለመቀበል እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ሀምሌ 21/2010 የኢትዮጵያ ሥነ-መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ከሌሎች ሀገራት ተቀብሎ ለማስተማር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ትምህርት ቤቱ ዛሬ በመደበኛ መርሃ ግብር በአምስት የተለያዩ ዘርፎች ያስተማራቸውን 39 ተማሪዎች አስመርቋል። የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ዶክተር ምስጋና ማቴዎስ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የሚሰሩ የውጭ ሀገር ዜጎች በትምህርት ቤቱ ተምረዋል። በቀጣይ ደግሞ በተለይ በዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎችን ከአፍሪካ ቀንድ፣ ከሰሜን አፍሪካ እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተቀብሎ ለማስተማር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት። ለዚህም የአለም አቀፍ ተማሪዎች መመሪያ እየተጠናቀቀ ሲሆን የመኝታ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች መዘጋጀታቸውንም ገልፀዋል። በፈረንጆቹ 2019/2020 በነዚህ ሀገራት ትምህርቶቹን የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም ነው ያስረዱት። ትምህርት ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ ሳምንት እስከ ሶስት ወር የሚቆዩ የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል። ስልጠናዎቹ በአመራርነትና ትምህርተ-መለኮትን ያጣመሩ፣ ፆታና ጤናን የተመለከቱ ሲሆኑ፤ በቀጣይ ዓመት እንደሚጀመሩም ነው የገለፁት። ዳይሬክተሩ ተመራቂ ተማሪዎች በአለምና በቤተክርስቲያኗ ያሉ የእግዚአብሄር ህዝብን እንዲያገለግሉም ጥሪ አቅርበዋል። ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው ከእውቀት በተጨማሪ ከትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በገበዩት ትህትና ሀገራቸውና ቤተክርስትያኗን እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሥነ-መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ከተመሰረተ 21 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን እስካሁን 550 ተማሪዎችን አስተምሮ ማስመረቁም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም