ቀጥታ፡

ግድቡ በመጪው ሐምሌና ነሃሴ ወራት 2ኛውን ዙር ውሃ የማይዝበት ምንም ምክንያት እንደሌለ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ

መጋቢት 8 / 2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጪው ሐምሌና ነሃሴ ወራት ሁለተኛውን ዙር ውሃ የማይዝበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግድቡ የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታና የግድቡን 10ኛ ዓመት የተመለከተ ውይይት ዛሬ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።

በዚህም ግድቡ ከወቅታዊ ሁኔታው፣ ከዲፕሎማሲ፣ ከማህበራዊና ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች አንጻር የሚኖረው ትስስር እንዲሁም ህጋዊና የቴክኒክ ጉዳዮችን የተመለከቱ የመነሻ ሃሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት የአምስት ዓመት ጊዜ በላይ በእጥፍ ጨምሮ በ10ኛ ዓመቱ የግንባታ አፈጻጸሙ 79 በመቶ ላይ ይገኛል።

የዲዛይን ችግር፣ የፋይናንስ እጥረት፣ ተጨማሪ ስራዎችና ሌሎችም ለግንባታው መዘግየት በምክንያትነት እንደሚጠቀሱ ነው የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የሚናገሩት።

ፕሮጀክቱ በዘገየ ቁጥር የግንባታ ወጪውም በዚያው ልክ እየጨመረ እንደሚሄድ ገልጸው፤ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ አጠቃላይ ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ጠቁመዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ለነበሩበት ችግሮች መፍትኤ በመስጠት ግንባታው እንዲፋጠን እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዘው ዕቅድ መሰረትም በዘንድሮ ክረምት ግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ መያዝ የሚያስችለው ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

“በዚህ መሰረት በመጪው ሐምሌና ነሃሴ ወራት ሁለተኛውን ዙር ውሃ ከመሙላት ወደ ኋላ የሚያስኬድ ምንም ምክንያት የለም” ብለዋል።

የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትኤ መፍታት በሚለው መርህ መሰረት ሶስቱ አገሮች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ድርድር ማድረግ ጀምረው ነበር።

ይሁንና ድርድሩ መቋጫ ካለማግኘቱ ባለፈ ግብጽና ሱዳን ሶስተኛ ወገን ጣልቃ እንዲገባ እያሳዩትት ያለውን ፍላጎት በተመለከተም “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መፍትኤ እንዲመጣ ከፍተኛ ፍላጎት አላት” ብለዋል።

የህብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር የዲሞክራቲክ ሪፐፕሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት አማካሪዎችና የቴክኒክ ባለሙያዎች የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ በሚያደርጉት ጥሪ መሰረት የሶስትዮሽ ድርድሩ በቅርቡ እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም