ቀጥታ፡

የሲሚንቶና የብረት እጥረት በግንባታ ሥራዎች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9/2013 (ኢዜአ) የሲሚንቶና የብረት እጥረት በግንባታ ሥራዎች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ገለጸ። ሥራ ተቋራጮች ሰራተኞቻቸውን የመበተን ስጋት ውስጥ መግባታቸውንም አመልክቷል።

ማህበሩ በግንባታ ኢንዱስትሪ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።   

የማህበሩ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ኢንጂነር የሱፍ መሐመድ እንደገለጹት ከፍተኛ የሰው ኃይል የተሰማራተበት የኮንስትራክሽን ዘርፍ  እየተባባሰ በመጣው የግንባታ አቅርቦት ችግር ላይ ወድቋል።

በተለይም ለግንባታ ወሳኝ የሆኑ የሲሚንቶና ብረት አቅርቦት እጥረት ጎልቶ እንደሚታይ አመልክተዋል።     

ሥራ ተቋራጮችም ለሰራተኞቻቸው ደሞዝ ለመክፈል መቸገራቸውን ገልጸዋል።

በግብዓቶቹ እጥረት ሳቢያም ፕሮጀክቶችን ለማቋረጥ እየተገደድን ነው ሲሉ ተናግረዋል።     

በዘርፉ  የተሰማራው የሰው ኃይል እንዳይበተን መፍትሄ እንዲፈለግም ምክትል ሊቀመንበሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ባንኮች ለተቋራጮች ቅድሚያ ክፍያ እንዳይፈጽሙ የጣለው እገዳ አሉታዊ ጫና ማሳደሩንም ተናግረዋል።

"ተቋራጮች ውሉ ላይ በ290 ብር ሲሚንቶ ቢሞላም፤ እስከ 700 ብር ሲሚንቶ ገዝቶ ሥራው እንዳይቋረጥ እየሰራ ነው። ከዚህ በላይ ምን ማድረግ ነበረበት?" ሲሉም ይጠይቃሉ።  

የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር  ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማሪያም፤ ዘርፉ ከገጠመው የግብዓቶች እጥረት ሌላ፤  ከባንኮች የሚወጣው ገንዘብ ላይ የተጣለው ገደብ ችግር ላይ ጥሎናል ብለዋል።

ችግሩን ለማቃለል ሥራ ተቋራጮችና ግብዓት አምራቾች በቀጥታ የሚገናኙበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ከ22 ሺህ በላይ ሥራ ተቋራጮች እንዳሉ ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም