እውነትና ንጋት--- - ኢዜአ አማርኛ
እውነትና ንጋት---
አብዱራህማን ናስር/ኢዜአ/
የሕወሓት ጁንታ ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የፌዴራል መንግስት በወሰደው እርምጃ ቡድኑ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ህልውናውን ወደ ማጣት ሲደርስ የተከተለው መንገድ የአክሱም ኤርፖርትን ጨምሮ ህዝብ የሚገለገልባቸው መሰረተ ልማቶችን ማውደም፣ በማይካድራና በተለያዩ አካባቢዎች ንፁሃንን መግደል፣ ዝርፊያዎችን መፈጸም ነበር። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ በማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በህወሃት ሚሊሻና ሳምሪ በተባለው ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል ነው ሲል መግለጹ ይታወሳል፡፡
ይህ የጥፋት ቡድን እነዚህንና መሰል ድርጊቶችን በመፈጸም ቀደም ሲል ባደራጃቸው የዲጂታል ወያኔ ሠራዊት እና በተባባሪዎቻቸው አማካኝነት የተለያዩ ምስሎችንና መረጃዎችን በመጠቀም የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በማህበራዊ ሚዲያ በኩል በስፋት አሰራጭቷል። የጁንታው ቡድን የዲጂታል ሠራዊት ያሰራጯቸው ምስሎች በአብዛኛው ከእውነታው ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውና በሌላ ሀገር የተፈጸሙ ድርጊቶች መሆናቸውን የአስቸኳይ ጊዜ የመረጃ ማጣሪያ ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አጋልጠዋል። ጋዜጠኛ ዓርአያ ተስፋ ማርያም በሰሞኑ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ የጁንታው ደጋፊዎች በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩት ተንቀሳቃሽ ምስሎች እራሱ የፈበረከው የሐሰት መረጃ ነው ሲል ገልጿል። የጥፋት ቡድኑን የበርካታ ዓመታት የጀርባ ታሪክ ለሚያውቅ ሰው ይህን መሰል የሀሰት መረጃ በማሰራጨቱ ሊያስደንቅ አይገባም በማለት የጁንታው ቡድን የቆየ ባህሪይ መሆኑን አክሎ ገልጿል።
እነዚህ የተሳሳቱና የተዛቡ መረጃዎች ሆን ተብለው በዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲወጡ ከመደረጉ ባሻገር ቡድኑ በስልጣን በነበረባቸው ረጅም ዓመታት በፈጠራቸው ትስስሮች እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በሰገሰጋቸው የቡድኑ አባላት አማካኝነት የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ ምክርቤት አባላትን ሎቢ በማድረግ መረጃዎችን አዛብቶ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። እንደማሳያ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በየቀኑ ሀሰተኛ ትርክቶችንና መረጃዎችን የሚያሰራጩ በሺዎች የሚቆጠሩ ትዊተርን ጨምሮ አዳዲስ የማህበራዊ ሚዲያ ገፆች በስፋት ሲከፈቱ ነበር።
መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች እንዲሁም አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ባሰራጯቸው የተዛቡ መረጃዎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ አድርዋል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በህዳር 2013 ዓ.ም አጋማሽ በሰጠው መግለጫ ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆኑ አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን የተሳሳቱ አሊያም ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎችን እያስተላለፉ መሆናቸውን ገልጾ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው እንደነበር ይታወሳል። ከእነዚህ መገናኛ ብዙሀን መካከል እንደ ሮይተርስ፤ ቢቢሲ አማርኛና እንግሊዝኛ፤ የጀርመን ድምጽ እና አልጀዚራ እንግሊዝኛ ይገኙበታል።
ዓለም አቀፉ የፖለቲካ ተንታኝ ጄፍ ፒርስ “Ethiopia vs. the New White Supremacy” በሚል ርእስ በፃፉት ፅሑፍ ምእራባውያን መገናኛ ብዙሃንና በሰብአዊ መብት ጥበቃ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች በአፍሪካ አህጉር ለነጭ የበላይነት ያቀነቅናሉ ሲሉ ኮንነዋቸዋል። እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ክራይስስ ግሩፕ የተሰኙ ድርጅቶች በምእራባውያን የገንዘብ ድጋፍ ስለሚንቀሳቀሱ በአፍሪካ ስላለው ጉዳይ ግድ አይላቸውም ሲሉ ገልጸዋል። ጄፍ ፒርስ “How Western Media (and others) are STILL failing Ethiopia” በሚል ርእስ ባስነበቡት ትንታኔ ደግሞ የህወሃት ጁንታ ቡድን አባላትና አጋሮቻቸው ለምዕራባውያን የሚዲያ ተቋማትና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ክፍያ በመፈጸም ህወሓት ለበርካታ አመታት ሲሰራ የቆየውን ግፍ በመሸፈንና በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ በይፋ ተችተዋል። ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን አውጥተው በአውሮፓና አሜሪካ ቅንጡ የመኖሪያ ቤቶችን የገነቡ ግለሰቦች በሚረጩት ገንዘብ ብዙ የሚዲያና የፖለቲካ ሰዎችን ከጎናቸው በማሰለፍ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ቀልብ ለመሳብ ቢችሉም እውነታው እየተጋለጠ መምጣቱን አያይዘው ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዲሁም የተለያዩ አክቲቪስቶች፣ ድርጅቶችና ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር ተረባርበዋል። እንደ ማርቲን ፕላውት፣ ትሮንቮል እና አብዲ ረሻድ የመሳሰሉትም በዚህ ዙሪያ በመደበኛነት ሲሰሩ ከርመዋል። እነዚህ ተቋማትና ድርጅቶች መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ እንዴት ተገዶ እንደገባ የሚያሳዩ በርካታ አስረጂዎችን ቢያቀርብም ብዙም ትኩረት ሊሰጡ አልፈለጉም። ከዚህ ይልቅ የጁንታው ቡድን አባላት በትዊተር የሚያሰራጯቸው የሀሰት ቅንብሮችን እንደትክክለኛ መረጃ አድርገው መጠቀምን መርጠዋል።
የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ በተመለከተ ተጨባጭነት በሌላቸው መረጃዎች ላይ በመመስረት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ለማቋረጥ እርምጃ ለመውሰድ የቀደመው አልነበረም። የአውሮፓ ህብረት በጥር ወር መግቢያ ባወጣው መግለጫ የፈረንጆቹ 2020 ከመጠናቀቁ በፊት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ከነበረው የበጀት ድጋፍ ውስጥ 90 ሚሊዮን ዩሮ እንዲዘገይ ውሳኔ አሳልፏል። ሕብረቱ የበጀት ድጋፍ ለማድረግ እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጣቸው አምስት ጉዳዮች ናቸው። እነዚህም የሰብአዊ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲገቡ፣ ሰላማዊ ሰዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት መጠጊያ ፍለጋ እንዲጓዙ ሲፈቀድላቸው፣ ብሔርን መሰረት ያደረጉ እርምጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ሲቆሙ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለመመርመር የሚያስችል አሰራር ሲዘረጋ እና መገናኛ ብዙሃን ወደ ትግራይ እንዲገቡ ሲፈቀድላቸው የሚሉ ናቸው። ድጋፉ የሚለቀቀው እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው ሲረጋገጥ እና እንደአስፈላጊነቱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ከግምት እየገቡ መሆኑን ገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት ያሳለፈው ውሳኔ በተሳሳተ ግምገማ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅቱ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል። ህብረቱ ያወጣው መረጃ መንግስት በክልሉ እያቀረበ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ ከግንዛቤ ያላስገባ እና በመረጃ ያልተደገፈ ነው ሲል የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መንግስት በአካባቢው የህግ ማስከበር ስራን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ህብረቱ የሚያወጣው መረጃ ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ እና ተገቢነት የሌለው መሆኑንም አመልክቷል። የአውሮፓ ህብረት እንደ ቀደምት መልካም አጋርነቱ ልማትና ሰላም በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ድጋፉን መቀጠል እንደሚገባው ገልጿል።
ፎሬይን ፖሊሲ መጽሄት “UNDP Memo Echoes Ethiopian Talking Points on Tigray” እንዳስነበበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በቅርቡ ለጸጥታው ምክር ቤት ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ አቅርቧል። በማስታወሻው ላይ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ሰብአዊ ኪሳራና አለመረጋጋት ሃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ትግራይን ሲመራ የነበረው ህወሃት እንደሆነ መገለጹን አስነብቧል። ሚስጥራዊ በተባለው በዚህ ማስታወሻ ሕወሃት በትግራይ ክልል በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ትንኮሳ መፈጸሙን ተገልጿል።
እንደ ፎሬይን ፖሊሲ ዘገባ የተመድ የልማት ፕሮግራም ባቀረበው ሰነድ ላይ የትኛውም አገር ወታደራዊ ጥቃት ሲደርስበት የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ የታወቀ መሆኑን በመጥቀስ በህወሃት ተንኳሽነት ምክንያት የተቀሰቀሰውን ችግር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተሳሳተ መንገድ በመረዳቱ ኢትዮጵያ ላይ አስፈላጊ ያልሆነ ጫና እያሳደረ መሆኑን አስገንዝቧል። ለጋሾችና የመብት ተማጋቾች ሁኔታውን ከማስጮህ ተቆጥበው በመልሶ ማልማትና በሰብአዊ እርዳታ ስርጭት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡንም መጽሔቱ ዘግቧል። መንግስት በትግራይ ክልል የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት በሚገባው ልክ አልተነገረለትም በማለት የሚወቅሰው የተመድ የልማት ፕሮግራም ሰነድ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ድጋፍ በመንግስት ትከሻ ላይ መውደቁንም ይጠቁማል።
የተመድ የልማት ፕሮግራም ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረበው ሰነድ በትግራይ ክልል ተፈጽሟል በሚል የሚነገረው ዘረፋ፣ ግድያና ጾታዊ ጥቃት የሕወሃት ቡድን ሽንፈት ሲያጋጥመው የለቀቃቸው ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ እስረኞችም ተሳትፎ እንዳለበት የሚያመለክት ሲሆን ቡድኑ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ በመቃወም መቀሌ ላይ መሽጎ ችግር ሲፈጥር እንደነበር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘብ ይገባል ይላል። የሕወሃት ቡድን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በማድረግ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው ጨቋኝ አገዛዝ ለመመለስ ሲሰራ እንደነበርም ሰነዱ ይጠቁማል። የሕወሃት ቡድን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እውቅና ያልሰጠው ህገ ወጥ ምርጫ ሲያካሂድ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ማለፉን በመውቀስ የቡድኑ ጥፋት በዚህ ሳያበቃ በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ሲፈጽም የሚመለከታቸው ተቋማትና ድርጅቶች አላወገዙም በማለት ይተቻል።
ከሰሞኑ የአውሮፓ ህብረት ያወጣው መግለጫ ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የተለየና መሻሻል የታየበት ነው። የአውሮፓ ህብረት በመግለጫው ኢትዮጵያን እንደቁልፍ አጋር እንደሚቆጥራት እና በአገሪቱ የሚካሄዱ የለውጥ ስራዎች እንደሚደግፍ ይፋ አድርጓል። የኢትዮጵያን ትክክለኛ እና ወቅታዊ ገፅታ ለመላው ዓለም ለማስተጋባት በኢትዮጵያውያን የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ህብረቱ እንደተመለከተው በማስታወስ ለአገሪቱ የሚያደርገውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል። መንግስት በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለመቅረፍ እያደረገ ያለውን ጥረት እውቅና እንደሚሰጥ የአውሮፓ ህብረት በመግለጫው ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ የተካሄዱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች እንደሚደግፍ በመግለጽ በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ተአማኒና ግልፅ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት የአውሮፓ ህብረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
የአውሮፓ ህብረት የአሁኑ መግለጫ ለማውጣት የተነሳሳው በሰሞኑ የተመድ የልማት ፕሮግራም ለጸጥታው ምክር ቤት ባቀረበው ማስታወሻ ላይ የተዘረዘሩ እውነታዎች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ያስተላለፏቸው መልእክቶች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በትግራይ ክልል በአካል በመገኘት መሬት ላይ ያለውን እውነታ መገንዘባቸውን ተከትሎ ነው ማለት ይቻላል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መንግስት፣ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እውነታውን ለማሳወቅ እያደረጉ በሚገኘው ጥረት ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ ያላቸው ጣልቃ ገብነት ለዘብ ማለቱን ገልጸዋል። እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ተቋማት እና በምዕራባውያን ዘንድ ውዥንብሮች ነበሩ። በዚህም ምክንያት በተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ይሁን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል አሜሪካ እና ምዕራባውያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት አሳይተዋል። ይሁን እንጂ እውነታው በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተገለጡ በመምጣታቸው ፍላጎታቸውን ማሳካት አልቻሉም። በቅርቡ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድ ጣልቃ መግባትን በመቃወም የቀረበው ረቂቅ ሰነድ ውድቅ መደረጉ የታወሳል።
በትግራይ ስላለው ሁኔታ “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል” እንደሚባለው በተለያዩ መንገዶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን ለማስገንዘብ በተሰራው ስራ በሂደት ለውጦች መታየት ጀምረዋል። የተመድ የልማት ፕሮግራም ሰነድ ላይ ስለትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የሕወሃት ማንነት የሚያሳዩ በርካታ እውነታዎች ተዘርዝረዋል። እነዚህ እውነታዎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትክክለኛና ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲይዝ የሚረዱ ናቸው።
በሌላ በኩል በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቀደም ሲል ከነበረው በተሻለ መልኩ በአንድነት በመሆን ድምጻቸውን ማሰማት በመጀመራቸው ተጽእኖ ማምጣት ችለዋል። በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ እና በአውስትራሊያ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመንግስታቱ ድርጅት እና ሌሎችም አካላት በሕወሃት ጁንታ ደጋፊዎች የሚሰራጨውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ተመርኩዘው በኢትዮጵያ ላይ እያሳደሩ ያሉትን ያልተገባና ኢፍትሃዊ ጫና እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት በተመድ ለአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ግሪኔልድ በጻፈው ደብዳቤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ገንቢ ሚና እንዲጫወት እና ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን እንዲቆም ጠይቋል።
እነዚህ ሁሉ ተደምረው ሲታዩ የሕወሃት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በሂደት እየተጋለጠ መምጣቱን በዚህም በተዛባ መረጃ ላይ ተመስርተው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አንዳንድ ተቋማትና ድርጅቶች እየለዘቡ መምጣታቸውን ያመለክታል። ይሁን እንጂ አሁንም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚሰሩ በርካታ ድርጅቶችና ተቋማት እንዳሉ መዘንጋት የለበትም። ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲደርስባት ሌት ተቀን የሚሰሩ አሉ። እነዚህ አካላት በቀጣይ ግንቦት ወር ለማካሄድ የታሰበው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዳይጠናቀቅ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። በመሆኑም ይህንን ወቅታዊ ሁኔታ ለመቀየር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በበለጠ ሀገራዊ አንድነታቸውን ማጠናከር ለነገ የማይባል ነው።