ቀጥታ፡

ሠላማዊና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሚጠበቅብንን እንወጣለን - በሲዳማ ተፎካካሪ ፓርቲዎች

ሀዋሳ፣  መጋቢት 08/2013( ኢዜአ ) ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሠላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ በሲዳማ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ካነጋገራቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲ.አ.ን) ዋና ፀሐፊ አቶ ለገሰ ላንቃሞ በክልሉ በሚገኙ 19ኙም የምርጫ ክልሎች ለፓርላማና ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ እጩዎችን ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲያቸው በፖለቲካ ትግል ውስጥ ረዥም ዓመት ያስቆጠረ እንደሆነ አስታውሰው እስካሁን በሠላማዊ መንገድ ሲታገል መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

“ባለፉት ሀገራዊ ምርጫዎች አፈና እንዲሁም መንግስትና ፓርቲ ያልተለዩበትን ሂደቶች አስተናግደናል” ያሉት ዋና ፀሐፊው ዘንድሮ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መኖራቸውንና በአዲስ የፉክክር መንፈስ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥና የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት ሳይደናቀፍ እንዲቀጥል ፓርቲያቸው ፅኑ ፍላጎት እንዳለው የተናገሩት አቶ ለገሰ “ምርጫው ያለ ምንም እንከን ሠላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል” ብለዋል፡፡

“የፓርቲው አመራሮችም ሆንን አባላት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ አክብረን እንቀሳቀሳለን” ብለዋል ፡፡

የሲዳማ ህዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሲ.ህ.አ.ዴ.ድ) ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጳውሎስ ፉላሳ በበኩላቸው በሁሉም የምርጫ ክልሎች እጩዎቻቸውን አቅርበው የምረጡኝ ቅስቀሳ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲያቸው ከዚህ በፊት በነበሩ አራት ዙር ምርጫዎች የሲዳማ ሀዲቾ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በሚል ስያሜ መወዳደሩን ገልፀው “አሁን ላይ ከጎሳ አስተሳሰብ በመውጣት መላው የሲዳማ ህዝብን ሊያቅፍ በሚችል ስያሜና አደረጃጀት ወደ ፉክክሩ ገብተናል” ብለዋል፡፡

“የሲዳማ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳድር መብቱ እንዲከበርለት ሁላችንም በሰላማዊ መንገድ ስንታገል ቆይተናል” ያሉት አቶ ጳውሎስ አዲስ በተደራጀው ክልል ውስጥ መፎካከር መቻላቸው መልካም የፖለቲካ መደላድል እንደሚፈጥርላቸው አመልክተዋል፡፡

ዴሞክራሲ ሂደት እንጂ በአንድ ጀንበር የሚመጣ እንዳይደለ ጠቅሰው “የዘንድሮውን ምርጫ በሁሉም ረገድ የተሳካ ፍፁም ፍትሀዊ ማድረግ ባይቻል እንኳ ባለፉት የምርጫ ሂደቶች የተስተዋሉ ችግሮችን ያረመና የተሻለ እንዲሆን የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

የሲዳማ አንድነት ፓርቲ (ሲ.አ.ፓ) ዋና ፀሐፊ አቶ መንክር ኃይለሚካኤል ደግሞ “ኢትዮጵያ ሠላማዊ የዴሞክራሲ ሽግግር ያስፈልጋታል” ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ በሁሉም ምርጫ ክልሎች የተወከሉ እጩዎችም ሆኑ ሌሎች የፓርቲው አባላት በሥነ-ምግባርና ደንብ ብቻ የተመራ እንቅስቃሴ በማድረግ ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን መወጣት እንዲችሉ ፓርቲው የግንዛቤ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን የህዝብን ድምፅ ማክበር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ  ለክልል 190ና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 19፣ የሲዳማ አንድነት ፓርቲ ለክልል 177ና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 19፣የሲዳማ ህዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ለክልል 135ና ለተወካዮች ምክር ቤት 17 እጩዎችን ማቅረባቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም