በአባይ ወንዝ 86 በመቶ አስተዋጽኦ ያላትን ኢትዮጵያ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብቷን ማንም አይነጥቃትም... አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
በአባይ ወንዝ 86 በመቶ አስተዋጽኦ ያላትን ኢትዮጵያ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብቷን ማንም አይነጥቃትም... አቶ ደመቀ መኮንን
መጋቢት 8 ቀን 2013 (ኢዜአ) “በአባይ ወንዝ 86 በመቶ አስተዋጽኦ ያላትን ኢትዮጵያ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብቷን ማንም ሊነጥቃት አይችልም” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስት አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 10ኛ ዓመት እየተከበረ ሲሆን የበዓሉ የመጀመሪያ መርሃ ግብር የሆነ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ይገኛል።
የግድቡ ግንባታ ሂደት 79 በመቶ መድረሱም በሲምፖዚየሙ ላይ ተገልጿል።
በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙት አቶ ደመቀ መኮንን ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ግድቡ የመላው ኢትዮጵያውያን አንጡራ ሃብት ነው።
ይህንን ሃብት ወደ ልማት ለመቀየርና ለመጠቀም ባለፉት 10 አመታት ኢትዮጵያውያን ብዙ ውጣ ውረድ ማለፋቸውን አስታውሰዋል።
“በአባይ ወንዝ 86 በመቶ አስተዋጽኦ ያላትን ኢትዮጵያ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብቷን ማንም ሊነጥቃት አይችልም” ሲሉም ተናግረዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እስከአሁን ዓለም ዓቀፍ የወሰን ተሻጋሪ ውሃ አጠቃቀም ህጎችን በማክበር መርህ ስትንቀሳቀስ መቆየቷን ገልጸዋል።ነገር ግን ከተደራዳሪ አገሮች ጋር በትብብር ለመስራት የምታደርገው ጥረት በጎ ምላሽ እያስገኘ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ‘ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል’ እንደሆነች አመልክተው፤ የፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ እንደምትሰራ ተናግረዋል።የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ያላቸው አገሮችም ተመሳሳይ የሆነ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ መከተል እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
እየተካሄደ ባለው ሲምፖዚየም የሶስትዮሽ የድርድር ሂደትን የሚዳስሱ የውይይት መነሻ ሃሳቦች በተደራዳሪዎች ቀርቦ ውይይት ይደረጋል።
በመድረኩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ተደራዳሪዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።