ቀጥታ፡

የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግሩን የሚያግዝ የዳታ ማዕከል በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ያግዛል የተባለ የዳታ ማዕከል በአዲስ አበባ በግሉ ዘርፍ ሊገነባ እንደሆነ ተገለጸ።

'አር.ኤፍ.ዲ.ሲ1' ተብሎ የተሰመው የዳታ ማዕከል ሬድ ፎክስ ሶሉሽንስ ግሩፕ በተሰኘ ኩባንያ በአዲስ አበባ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ እንደሚገነባ ታውቋል።

የዳታ ማዕከሉ ግንባታ ማስጀመሪያ ይፋ ሲደረግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝን ጨምሮ ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ተገኝተዋል።

"ማዕከሉ የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር የሚያግዝ ነው" ያሉት ዶክተር ኢዮብ፤ ዲጂታል ኢኮኖሚ መገንባትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም ዘርፍ ማልማት የኢትዮጵያ ትኩረት እንደሆነ ገልጸዋል።

ዲጂታል ኢኮኖሚ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕከል እንደመሆኑ ዋናው መሰረቱ ዘመኑን የሚመስል የዳታ ማዕከል እንደሆነ ገልጸዋል።

"ይህ ከሆነ የተማረ ወጣት በስፋት ማፍራትና በመቀጠልም ፌስቡክ፣ ትዊተርና ሌሎች መተግበሪያዎችን በአገር ውስጥ ማበልፀግ ያስችላል" ብለዋል።

የአገሪቷን የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ለማዘመን ማዕከሉ ትልቅ ጥቅም እንዳለውም ጠቅሰዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ዳታ የአጠቃላይ ኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ኢዮብ፤ የዳታ ማዕከሉ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መገንባትም የመንግስትን ጫና እንደሚያቃልል አመልክተዋል።

የሬድ ፎክስ ሶሉሽንስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አዳነ ካሳዬ በበኩላቸው ኩባንያው ዘመኑን የሚመጥን የዳታ ማዕከል እንደሚገነባ አረጋግጠዋል።

የተለያዩ ምዕራፎች ያሉት የማዕከሉ ግንባታ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ ይሁንና ለአገሪቷም ሆነ ለተለያዩ ኩባንያዎች ከወጪ አንጻር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።

"ኢትዮጵያ ወደፊት የውሃ ሀይል አመንጭታ ለመላክ ትልም ያላት እንደመሆኑ የዘርፉ አንቀሳቃሾች አስፈላጊ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል" ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም