በሆስፒታሎች የህክምና የግብዓትና የመድሀኒት እጥረት ለመፍታት እየተሰራ ነው -የአማራ ጤና ቢሮ

ደሴ፣ መጋቢት 7/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በሆስፒታሎች የህክምና ግብአትና የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት በመፍታት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡

"እኔምያገባኛል" የተሰኘ የተቋማት ለውጥ ትግበራ አዲስ አሰራር መርሀ ግብር  በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማስጀመር ውይይት ተካሂዷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሎች በህክምና ግብዓትና የመድሃኒት እጥረት ችግር በሚጠበቅባቸው ልክ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡

በተለይ በአንዳንድ ሆስፒታሎች በቂና የሰለጠነ የጤና ባለሙያ እያለ በጥቃቅን የግብዓት ችግር የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ አለመቻሉን ጠቁመው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሆስፒታሎች የግብዓት አቅርቦት ክፍተት ተሟልቶ በቂና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ "ያገባኛል" የሚል አዲስ አሰራር መርሀ ግብር የጤና ተቋማት ለውጥ ትግበራ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በግብአት አቅርቦት ክፍተት ከደረጃ በታች አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎች ተለይተው ችግራቸውን በመፍታት  ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

እየገጠመ ያለውን ከፍተኛ የመድሃኒት እጥረት ችግር ለመፍታት  ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ድርጅት በተጨማሪ በአምባሰል ንግድ ስራዎች በኩል ከውጭ ለማስገባት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በበኩላቸው የሆስፒታሎች ሁለተናዊ ችግር ተቀርፎ ለህብረተሰቡ በቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡

 የክልሉ መንግስት በጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁሳቁስና የመድሃኒት እጥረት ችግርን በሚችለው አቅም በአፋጣኝ እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጦ ለአፈጻጸሙ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

"አዲስ የተጀመረው የ"ያገባኛል" መርሀ ግብር ሁሉንም አነሳስቶ በሚችለው ልክ የመፍትሄ አካል እንዲሆን እድል ይፈጥራል" ያሉት አፈ ጉባኤዋ ውጤቱ እየታየ ሌሎች ሆስፒታሎችም በመርሀ ግብሩ እንዲታቀፉ እንደሚደረግ ጠቁመዋል ።

በትግራይ ክልል በተወሰደው ህግ ማስከበር ዘመቻም አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ሆስፒታሎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም ከፌደራል መንግስት ጋር እየተሰራ መሆኑን ዋና አፈ ጉባኤዋ አስታውቀዋል፡፡

በኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ጀነራል ዶክተር ያእቆብ ሰማን "በሀገር ደረጃ 24 ሆስፒታሎች ''በያገበኛል'' አዲስ አሰራር ታቅፈው ችግራቸው ተለይቷል" ብለዋል፡፡

"ሆስፒታሎቹ ችግራቸው በየደረጃው ተፈቶ የሚመጥናቸውን አገልግሎት ለህዝብ እንዲሰጡ ይደረጋል" ያሉት ዶክተር ያዕቆብ በሂደት በሌሎች ሆስፒታሎችም መርሃ ግብሩ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

ከጤና ጠቢያ በታች አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎች መኖራቸውን ጠቁመው ጤና ሚኒስቴር  ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ደረጃቸውን በማሻሻል ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጡ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይድ ሆስፒታል ተወካይ ስራ አስኪያጅ አቶ አንዋር ጀማል በበኩላቸው "ሆስፒታሉ ለምስራቅ አማራ፤ ለአፋርና ለትግራይ ክልሎች በከፊል ከ8 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ተደራሽ ቢሆንም በቦታ ጥበት፤ በህክምና ቁሳቁስና በመድሃኒት እጥረት በሚጠበቅበት ልክ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም" ብለዋል።

"የሰለጠነ የጤና ባለሙያ እያለ ህሙማን ሲሞት እንደመመለክት የሚያሳዝን ጉዳይ የለም ያሉት ስራ አስኪያጁ በተጀመረው መርሃ ግብር ችግሩ ይቀረፋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በሆስፒታሉ ለመርሃ ግብሩ ማስተግበሪያ 866 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በጥናት መለየቱን ጠቅሰው በፌደራል፤ በክልሉና በሆስፒታሉ አቅም በጀቱን ለማሟላት ታስቦ ትግበራው መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አማካሪዎችን ጨምሮ ከፌደራል፤ ከክልልና ከደሴ ከተማ የተውጣጡ አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ተጎብኝቷል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም