አሜሪካ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን የለውጥ እርምጃ አደነቀች

60
አዲስ አበባ ሐምሌ 21/2010 የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሚያደርጉትን የለውጥ እርምጃ አደነቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ጋር በኋይት ኃውስ ተወያይተዋል። ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ውይይቱን ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው ''ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን በማግኘቴ ክብር ተሰምቶኛል'' ሲሉ ገልጸዋል። የሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ የንግድ ግንኙነቱ እንዲሻሻልና ከኤርትራ ጋር ሠላም እንዲሰፍን ያደረጉትን ታሪካዊ የማሻሻያ ርምጃዎች አድንቀዋል። በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ ጋር በዋሺንግተን ዲሲ ተወያይተዋል። ክርስቲን ላጋርድም በትዊተር ገጻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ተቀብለው ማነጋገራቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ውይይታቸውም ፍሬያማ እንደነበረና ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ የፈረሙትን የሠላም ድንጋጌ በተመለከተም የ'እንኳን ደስ አልዎ' መልዕክት ማስተላለፋቸውን ጠቁመዋል። በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ እየወሰዱ ላለው የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ ርምጃ አድናቆት እንዳላቸው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ቀጣይና ሁሉን አቀፍ ልማት እንዲረጋገጥ በማድረግ ድህነትን ለመቀነስ ተቋማቸው ከመንግሥት ጋር አብሮ እንደሚሰራም አረጋገጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ጂም ዮንግ ኪም ጋር በተመሳሳይ በዋሺንግተን ዲሲ ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸውም ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰብዓዊ ልማት ላይ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኛ እንደሆነና የሚገኘውን ኃብት በሙሉ የኢትዮጵያውያንን ህይወት ለመለወጥ እየሰራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፤ ለዚህም ደግሞ ባንኩ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ጂም ዮንግ ኪም በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ይፋ ያደረጓቸውን የፖሊሲ አቅጣጫዎች በቅርበት መከታተላቸውን ጠቅሰዋል። ይህንንም ዓለም ባንክ እንደሚያደንቅ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም