ቀጥታ፡

ለደንገጎ አካባቢ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ፕሮጀክት 10 ሚሊየን ብር ተመድቦ እየተሰራ ነው

ሐረር፤ መጋቢት 07/2013(ኢዜአ) ፡- በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ደንገጎ አካባቢ ለሚካሄድ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ፕሮጀክት 10 ሚሊየን ብር ተመድቦ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና  የደንገጎ ዛፍን መሰረት በማድረግ  መልሶ የማልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ፤ ዶክተር  ተሰማ ቶሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ በዋናነት ደንገጎ አቅራቢያ የሚገኘው የአደሌ ሀይቅን ማዕከል በማድረግ በዙሪያውን 11 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን ነው።

በዚህም የተፈጥሮ ሃብት ልማትና  ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በአካባቢው የተጎዳውን የተፈጥሮ ሃብቱን መልሶ እንዲያገግም፣  ድሬዳዋ የሚከሰተውን ጎርፍ ማስቀረት እና  የእርሻ ስራን በማጎልበት የአርሶ አደሩን   ምርታማነት እንዲጨምር ያስችላል ብለዋል፡፡

10 ሚሊየን ብር በመመደብ የፕሮጀክቱን  ስራ እያከናወኑ የሚገኙት  የፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን እንዲሁም ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ስራ ከተጀመረ ሁለት ወራት እንደሆነው ያመለከቱት ዶክተር ተሰማ እስካሁንም በየደረጃው የተለያዩ ኮሚቴዎች የማዋቀር፣ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ የመስጠት እና ቦታውን የማካላል ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንግስቱ ኡርጌ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አየር ንብረት እንዲስተካከልና የአደሌ ሀይቅ የውሃ መጠን እንዲጨምር እገዛ ያደርጋል እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር በየጊዜው የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ እንዲቀንስ ከማስቻል ባሻገር የደንገጎ አካባቢ መልሶ በመልማት ለሐረር፣ሀረማያ፣ድሬዳዋና አካባቢዎች እንደ መዝናኛነት ያገለግላል ብለዋል፡፡

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢ ሲተገበርም ደንገጎና አካባቢው ተመራጭ ስፍራ ለማመቻቸትም እንደሚያግዝ አመላክተዋል፡፡

በሐረማያ ወረዳ ደንገጎ ቀበሌ ገበሬ በማህበር ቢፍቱ ተፋሰስ ላይ ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክት ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ያሉት ደግሞ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፈዲላ ዳውድ ናቸው ፡፡

በተለይም ከ17 ዓመታት በኋላ የተመለሰው የሀረማያ ሀይቅ እንዳይርቅ ጭምር እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ለማድረግም የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ከዞን ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለአርሶ አደሩና ሌላውም ህብረተሰብ ስልጠና በመስጠት የህዝብ ፕሮጀክት ለማድረግ ተስፋፈቶ የሚቀጥል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦና ያደሳ በበኩላቸው፤ በክልሉ በተለይም የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲለሙ እና በደን የተሸፈኑ ስፍራዎችም ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ደንገጎን መልሶ የማልማት ስራ በክልሉ በተጠና መልኩ እየተከናወኑ ካሉ ሁለት ሞዴል ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ያሉት አቶ ቦና፤  ለማስፈጸምም   መስሪያ ቤታቸው፣ የፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽን እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መካከል የሶስትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም