በርበሬ፣ ሽሮ እና ቆሎን ጨምሮ ለስድስት አገር በቀል ምግቦችና መጠጦች የጥራት ደረጃ ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
በርበሬ፣ ሽሮ እና ቆሎን ጨምሮ ለስድስት አገር በቀል ምግቦችና መጠጦች የጥራት ደረጃ ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7/2013 ( ኢዜአ) በርበሬ፣ ሽሮ እና ቆሎን ጨምሮ ስድስት አገር በቀል ምግቦችና መጠጦች የጥራት ደረጃ እንደተዘጋጀላቸው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
ኤጀንሲው ከኢትዮጵያ ምግቦችና መጠጦች መካከል በርበሬ፣ ሽሮ፣ ቆሎ፣ ጠጅ፣ የአበሻ አረቄና ጠላ ተገቢውን የጥራት ደረጃ አሟልተው ለገበያ እንዲቀርቡ ለማድረግ ጥናት ተጠናቆ ለደረጃዎች አርቃቂ ኮሚሽን መቅረቡን አስታውቋል።
የአገሪቷ ምርቶች በዘመናዊ መንገድ ተዘጋጅተውና ጥራታቸውን ጠብቀው ለገበያ እንዲቀርቡ ደረጃ የማውጣት ስራዎች መከናወናቸውን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳወቅ መኮንን ለኢዜአ ገልፀዋል።
ለጤና ተስማሚ የሆኑ የበርካታ ምግቦች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ እነዚህን ሀብቶቿን ደረጃ እንዲያገኙ በማድረግ በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ምግቦችን በማቅረብ ተጠቃሚ አለመሆኗን አንስተዋል።

በመሆኑም ለምግቦቹና መጠጦቹ ደረጃ ለማውጣት መሥፈርቶች መዘጋጀታቸውንና ምግቦቹም ሆኑ መጠጦቹ የያዙትን ንጥረ ነገር፣ ለጤና ተስማሚነታቸውና ጥቅማቸውን የሚሳይ ማብራሪያ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡
ለተጠቀሱት ምርቶች ደረጃ ለማውጣት የተካሄደው ጥናት ለቴክኒክ ኮሚቴ መቅረቡንና በዚህ ዓመት ፀድቆ ስራ ላይ እንደሚውልም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
የደረጃው መውጣት በተለይ በአገር ውስጥ ከምርቶቹ ጋር የሚቀላቀለውን ባዕድ ነገር ለመከላከል ከፍያለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ስነ-ምግብ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ማሽረሻ ተሰማ በበኩላቸው ለአገር በቀል ምግቦች የጥራት ደረጃ መዘጋጀቱ አገሪቷን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የሚኖረውን ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡

አገር በቀልና ባሕላዊ ምግቦችን የጥራት ደረጃቸውን ጠብቆ ማውጣት ለአገር ኢኮኖሚ የሚኖረው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ በስፋት የሚመረቱትን እነዚህን ምግቦችና መጠጦች በዓለም አቀፍ ደረጃ በማቅረብ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ይቻላል ብለዋል።

ለሚያዘጋጇቸው የባልትና ውጤቶች ደረጃ እንዲወጣላቸው ለረጅም ጊዜ የሚመለከተውን አካል ሲጠይቁ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የበፍረኮት ባልትናና ቅመማ ቅመም ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ ኡመር ናቸው፡፡
በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ከፍተኛ የምርቶቹ ፍላጎት በመኖሩ በርካታ ጥያቄዎች እንደሚመጡ ጠቅሰው የደረጃዎች መውጣት ምርቶቻቸው በአውሮፓም ገበያ እንዲገቡ እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል፡፡