ቀጥታ፡

በሕዳሴ ግድብ ላይ የሶስትዮሽ ድርድር የሚቋጨው በሶስቱ አገሮች እንጂ በአደራዳሪዎች አይደለም - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

መጋቢት 7 /2013 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ የሶስትዮሽ ድርድር የሚቋጨው በሶስቱ አገሮች እንጂ በአደራዳሪዎች እንዳልሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመለከተ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የወቅቱን አበይት ሳምንታዊ ክንውኖች በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

“የአደራዳሪ ሚና ማስተባበር እንጂ ማጉረስ አይደለም” ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ሱዳንና ግብጽ አራት አደራዳሪ ወገኖች ይግቡ በሚል ያቀረቡት ሃሳብ ለኢትዮጵያ በይፋ እንዳልቀረበ ገልጸዋል።

አደራዳሪነት ማስተባበር እንጂ ውይይቱ የሚቋጨው በሶስቱ ተደራዳሪዎች እንደሆነ በስምምነት ሰነዱ መቀመጡን ገልጸዋል።

“ለአፍሪካ ህብረት ትልቅ ክብር አለን፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ የመፍታት ፅኑ አቋም አላት” በማለት ተናግረዋል።

“በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ጉዳይ ኢትዮጵያ ዝም አላለችም፣ ውስጥ ለውስጥ ዲፕሎማሲዊ ስራ እየሰራች ነው” ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ግብፅና ሱዳን ብዙ ነገር እንደሚሉ አብራርተዋል።

“ኢትዮጵያ ለድርድር ሁሌም ዝግጁ ናት። ሙሌቱም ይቀጥላል። ድርድሩ ግን ከሙሌቱ በፊትም ቢሆን ቢቋጭ ኢትዮጵያ ችግር የለባትም” ብለዋል።

ሱዳንና ግብጽ በሶስትዮሽ ድርድሩ ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ እንዲገቡ ፍላጎት እንዳላቸው ማስታወቃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም