ቀጥታ፡

6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የምክር ቤት አባላት ተገለጹ

ባህርዳር፤ መጋቢት 6/2013 /ኢዜአ/  ስድሰተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በክልሉ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የአማራ ክልል ምክርቤት አባላት ገለጹ።

ከምክርቤቱ አባላት መካከል ከደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ ተወካይ አቶ ጌታቸው አሊ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ምክር ቤቶች ከዴሞክራሲ ተቋማት አንዱ በመሆናቸው አባላት ያለሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ስለምርጫው አስፈላጊነት ለህዝቡ ግንዛቤ በመፍጠር የሚፈልጉትን ፓርቲ በካርዳቸው በመምረጥ ወደ ስልጣን በማውጣት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጎልበት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እኔም ወደ ወከልኩት ወረዳ ስመለስ የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡን በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የአካባቢያችን ባህል፣ ወግና እሴት ጠብቀው በመወዳደር ለማሸነፍ የፖሊሲ አመራጮች ላይ የተመሰረተ ውይይት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

ከግጭት ቀስቃሽና ጥላቻ ንግግር በመቆጠብ የሰለጠነ የፖለቲካ ቅስቀሳ ማካሄድ ለሀገር አንድነትና ህዝብ ደህንነት አስፈላጊ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች መገንዘብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ከማዕከላዊ ጎንደር የተወከሉት የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ይመኝ አድማሱ በበኩላቸው ከዚህ በፊት የተካሄዱት ምርጫዎች የአማራን ህዝብ በተሳሳተ ትርክት ችግር ውስጥ በነበረበት የተካሄዱ ናቸው ብለዋል።

የዘንድሮው ምርጫ የጥላቻ ምንጭ የሆነው ህውሃት በተወገደበትና በየአካባቢው ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተመለሱበት ማግስት የሚካሄድ በመሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።

የምክርቤት አባላትም ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ ህዝቡ የምርጫ ካርድ በማውጣት ይወክለኛል ያለውን ፓርቲ እንዲመርጥ የማስተማርና ግንዛቤውን የማሳደግ ሃላፊነታችን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።

ህብረተሰቡ በካርዱ በሚመርጠው ፓርቲ እንዲተዳደር እየሰራን እንገኛለን ያሉት ደግሞ ከሰሜን ሸዋ ዞን የተወከሉት የምክርቤት አባል አቶ ንጉስ ካሴ ናቸው።

መጪው ምርጫ ከሂደቱ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ህዝቡን በማስተባበር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ወደ ምክርቤቱ ጉባኤ ከመምጣታቸው በፊትም ወጣቶች በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች በመሄድ ስለምርጫው አስፈላጊነት ግንዛቤ ለማስጨበት ጥረት ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ወጣቱ ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ የሚያነሳቸው ጥያቄ ቢኖሩም ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የሁሉም ፍላጎት መሆኑን አረጋግጠዋል።

በስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ብልጽግናን ጨምሮ 47 የፖለቲካ  ፓርቲዎች እንዲሁም 125 የግል ዕጩዎች ለመወዳደር መቅረባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም