ቀጥታ፡

የተከበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚሰራ ኢዜማ ገለጸ

ደብረብርሃን፤ መጋቢት 06/2013(ኢዜአ) ዴሞክራዊያዊ ስርዓት እና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ / ገለጸ።

ፓርቲው “ንቁ ዜጋ ምቹ ሀገር” በሚል መሪ  ሀሳብ  የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱን በደብረብርሀን ከተማ  ለአባላቱና ደጋፊዎቹ  አስተዋውቋል፤ የምርጫ ቅስቀሳም አካሄዷል።

በትውውቅ መድረኩ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ እንዳሉት፤ኢዜማ በምርጫው ቢያሸንፍ ፓርላሜንታዊ ስርዓትን ወደ ፕሬዝዳንታዊ የመቀየርና ህገመንግስቱን በማሻሻል ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚኖርባትን ሀገር ለመፍጠር ይሰራል።

ሀገሪቱን መለወጥ የሚያስችል፣ የዜጎችን ተጠቃሚነትና እኩልነትን የሚያረጋግጡ 42 ፖሊሲዎች መቀረፃቸውን ተናግረዋል።

ግብርናውን ለማዘመን  በመስኖ አውታሮች ላይ በመመስረት ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም በየአምስት ዓመቱ የሚጠኑ የጤና፣ አካባቢ ጥበቃና ትምህርት ፖሊሲዎችን ፓርቲው መቅረጹንም ገልጸዋል።

በውጪ ጉዳይ ፖሊስም ረገድ ኢቨስትመንትን በመሳብ ላይ የተመሰረተ የሀገራችን መብት ጥቅም የሚያስጠብቅ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

ፓርቲው ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፓርቲያቸው በምርጫው ቢሸነፍም አሸናፊው ፓርቲ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን እየተከታተለ የሚያርም በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ "ጥላ ካቤኔ" እናደራጃለን ሲሉ አስታውቀዋል።

በምርጫ ምክንያት ምንም ዓይነት ግጭት እንዳይከሰት ፓርቲው አብክሮ እየሰራ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ጫኔ 1ሺህ 385 እጩዎችን ለህዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤት ማቅረባቸውንም ይፋ አድርገዋል።

ህዝቡ ለምርጫው በነቂስ ወጥቶ የሚበጀውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችለውን ካርድ በመወሰድ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

በፓርቲው የፖሊሲ ጥናት ባለሙያ ዶክተር ሙሉአለም ተገኘወርቅ በበኩላቸው የፓርቲያቸው የመጨረሻ ቃል ኪዳን ኢትዮጵያ በመሆኑ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ አለሙ ዘውዴ በሰጡት አስተያየት፤ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም