ቀጥታ፡

አምባሳደር አድማሱ ጸጋዬ በኢንዶኔዢያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አምባሳደር ጋር በወቅታዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

መጋቢት 6 /2013 (ኢዜአ) በኢንዶኔዢያ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉስልጣን አምባሳደር ፕሮፌሰር አድማሱ ጸጋዬ በኢንዶኔዢያ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አምባሳደር ከሆኑት አብዱላ ሳሊም አል ዳህሪ ጋር በወቅታዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

አምባሳደሮቹ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ካካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ እያከናወነ የሚገኘውን የመልሶ ግንባታ እና የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች የዳሰሱ ሲሆን ፕሮፌሰር አድማሱ በዚህ ወቅት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እንዲሁም የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ ስላለው ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ በማካሄድ ላይ ያለችውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስት ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍም አምባሳደሩ ምስጋና አቅርበዋል።

አምባሳደር አብዱላ ሳሊም አል ዳህሪ በበኩላቸው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስት ከኢትዮጵያ ጎን ሆኖ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምታካሂደውንም የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍም መንግስታቸው እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢንዶኔዢያ ጃካርታ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም