ለወጣቶች አለመግባባትን በውይይት መፍታትን ማስተማር ይገባል - ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ለወጣቶች አለመግባባትን በውይይት መፍታትን ማስተማር ይገባል - ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5 ቀን 2013 (ኢዜአ) ወጣቶች አለመግባባትን በውይይት መፍታት እንዳለባቸው የእምነት ተቋማት ሊያስተምሯቸው እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከብሯል።
በመርኃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፤ "ካውንስሉ ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግ በተግባር አሳይቷል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ከመንፈሳዊ ተልዕኳቸው ጎን ለጎን በርካታ ለአገር ልማትና እድገት አሻራቸውን ማኖር መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ትምህርት እንዲስፋፋና መሰረተ-ልማት እንዲጠናከር እነዚህ የእምነት ተቋማት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አንስተው፤ ምስጋና እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ያም ሆኖ ተቋማቱ አሁንም በተለይም በአገሪቷ የሠላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን አስተዋጽኦ ይበልጥ በማጠናከር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
"እንጋጭ ካልን በርካታ የሚያጋጭ ነገሮች አሉ" ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ በተለይም ወጣቶች በሚያግባቡና ትልቁ ስዕል "አገር" ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ወጣቶች አለመግባባትን በውይይት እንዲፈቱና የሃይማኖት አባቶችን መስማት እንዲያዘወትሩ አበክሮ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"የእምነት ተቋም የሞራል አቅጣጫ መጠቆሚያ ኮምፓስ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ወጣቱ ትውልድ ለሚፈራው አካል ተገዥ የመሆን ስብዕና ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው "የሰው ልጅ ከጥፋቱ ሊመልሰውና ከስህተቱም ሊያርቀው የሚገባና ሠላማዊ እንዲሆን የሚያስችለው ህሊና ያስፈልገዋል" ብለዋል።
የእምነት ተቋማት የሕዝቡ ዋነኛ ህሊና መሆኑን ገልጸው፤ በማኅበረሰብ ውስጥ እኩልነት፣ አብሮነት፣ መተባበር፣ ፍቅርና ይቅርታ እንዲዳብሩ እንደሚያስችሉ ጠቁመዋል።
አሁንም የእምነት ተቋማት በአገሪቷ እነዚህ በጎ እሴቶች ይበልጥ እንዲያብቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ካውንስሉ በመተባበርና በአንድነት ውስጥ ሃይል መኖሩን እንዲሁም የማይቻል ነገር አለመኖሩን በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።
ይህንን መተባበርና አብሮነት ከሌሎች የእምነት ተቋማትም ጋር በመፍጠር አገሪቷ የሚገጥሟትን ችግሮች ለማለፍ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚቻልና አገሪቷ ያሰበችው ቦታ ላይ ለመድረስ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
የእምነት ተቋማት በተለይም ማኅበረሰቡን መልካም እሴቶች በማስተማርና ሥነ ምግባር ያለው ትውልድ በመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የካውንስሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ቄስ ዶክተር ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው ካውንስሉ ባለፈው አንድ ዓመት የመደራጀት ሥራ ላይ መቆየቱን አውስተው፤ በቀጣይ ዓመታት ሃይማኖታዊና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶቹን ለመከወን ከወዲሁ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በሥሩ አስር አብያተ-ክርስቲያናትን ያቀፈ ነው።