የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር 32ኛውን ዓመታዊ የጥናት ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር 32ኛውን ዓመታዊ የጥናት ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር 32ኛውን ዓመታዊ የጥናት ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ።
በዘርፉ አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ ሙያተኞችም ዕውቅና ተችሯቸዋል።
ጉባዔው የጤናው ዘርፍ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
መርሐ ግብሩን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በይፋ ከፍተዋል።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ "ጉባዔው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት መካሄዱና ተሳታፊዎችም በአካል ብቻ የማይሳተፉበት መሆኑ ከወትሮው ለየት ያደርገዋል" ብለዋል።
"በኮቪድ-19 ወቅት ማኅበሩ የተሻለ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ እንዲሻሻል ጥረት አድርጓል፤ ለአባላቱ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ሰርቷል" ብለዋል።
ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ማኅበሩ ለጤናው ዘርፍ ብልፅግና ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው አንስተዋል።
ለአብነትም ስልጠናዎችን በማዘጋጀትና የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በሚያስችሉ ፖሊሲና መመሪያ ቀረፃ ተሳትፎው ጉልህ እንደነበር አንስተዋል።
ከዩኒቨርሲቲዎችና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የምርምር ስራዎችን መስራቱንና የስነ ተዋልዶና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ላይ መስራቱን ጠቅሰዋል።
ለጤና ዘርፍ ሁሉን አቀፍ መሻሻል የማኅበሩ አባላት የማይተካ ሚና እንደነበራቸው ገልፀው፤ የነበረውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ማኅበሩ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሙያ ማኅበራት እንዲጠናከሩ ጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
ጉባዔው የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጠቃሚ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበትና ውጤታማ እንዲሆን ተመኝተው በይፋ ከፍተውታል።
በዓመታዊው ጉባዔ መክፈቻ በኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ውጤታማ አገልግሎት ለሰጡ የጤና ባለሙያዎች ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
ከእነዚህ መካከል አቶ ወርቅነህ ካሴና ፕሮፌሰር መላከብርሐን ዳኘው በዘርፉ ላበረከቱት አገልግሎት ማኅበሩ የ'ከፍተኛ የኅብረሰተብ ጤና አገልግሎት'፤ ዶክተር አበባው ፈቃዱ ደግሞ የ'ከፍተኛ የኅብረተሰብ ጤና ተመራማሪ' ሽልማት አበርክቶላቸዋል።
አቶ አማረ ታሪኩ የ'ወጣት የኅብረተሰብ ጤና ተመራማሪ' ሽልማት አግኝተዋል።
ለሶስት ቀናት በሚዘልቀው ጉባዔ ኮቪድ-19ን ጨምሮ በተለያዩ ጤና ነክ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ።