ቀጥታ፡

በክልሉ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ እንዲሆን የሚያስችል ነው- ኢዜማ

ባህር ዳር)፣ መጋቢት 5/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው እንዲሆን የሚያስችል ነው ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ።

ፓርቲው ለኣባላቱና ደጋፊዎቹ ፕሮግራሙን ያስተዋወቀበትና የምርጫ ቅስቀሳ ያደረገበትን መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ አካሂዷል።

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ በወቅቱ እንደገለጹት ኢዜማ በመጭው ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ ለማሸነፍ የሚያስችለውን ዝግጅት አድርጓል።

የአማራ ክልል መንግስት ተፎካሪ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን የማስተዋወቅና የምርጫ ቅስቀሳቸውን በአደባባይም ሆነ በአዳራሽ በነጻነት እንዲያካሂዱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የተፈጠረው መልካም ጅምር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል። 

"በክልሉ የታየው ነጻ የፖለቲካ ምህዳርም የዘንድሮን ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው በማድረግ ልክ እንደ አደዋ ድል ሁል ጊዜ ሲታወስ የሚኖር የሚያደርገው ነው" ብለዋል።

ኢዜማ ምርጫውን ለማሸነፍ የሚያስችለውን ፕሮግራም በመቅረጽ ለመላ አባላቱና ደጋፊዎቹ ማስተዋወቁን ጠቁመው "አሁን ላይ የህዝብ ድምጽ ለማግኘት የሚያስችለውን የምርጫ ቅስቀሳ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ 547 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በ448ቱ ለመወዳደር የሚያስችለውን እጩ ማቅረቡን ጠቁመው "ፓርቲው በሚወዳደርባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግንባር ቀደም ያደርገዋል" ብለዋል።

ፓርቲው የህዝብ ይሁንታ አግኝቶ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ መመረጥ ከቻለ መንግስት ለመሆን የሚያስችለውን አደረጃጀት ዘርግቶ እየተንቅሳቀሰ እንደሚገኝ አቶ የሺዋስ አስታውቀዋል። 

"ፓርቲው ከሁሉም በፊት የሀገርን ሰላምና አንድነት የሚያስቀድም በመሆኑ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በየደረጃው ካሉ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ተከታታይ ውይይት እያካሄደ ይገኛል" ብለዋል።

ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት አቶ የሺዋስ "ሰላምን የማስከበር ጉዳይ በዋናነት የገዥው ፓርቲ ቢሆንም ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው" ሲሉ አመላክተዋል።

ኢዜማ ትላናንት ማምሻውን በባህርዳር ከተማ በዋና ዋና ጎዳናዎች በተሽከርካሪ የታገዘ የምርጫ ቅስቀሳ ያካሄደ ሲሆን ዛሬ ጧት ደግሞ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር በሙሉ አለም አደራሽ ውይይት አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም