ማስ ስፖርትን ለጤናማ ማኅበረሰብ ግንባታና ማኅበራዊ ትስስር መጠቀም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ማስ ስፖርትን ለጤናማ ማኅበረሰብ ግንባታና ማኅበራዊ ትስስር መጠቀም ይገባል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5/2013(ኢዜአ) የማስ ስፖርትን ለጤናማ ማኅበረሰብ ግንባታና ማኅበራዊ ትስስር መጠቀም እንደሚገባ ተነገረ።
በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች "የማስ ስፖርት" የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ይካሄዳሉ።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከል "በስፖርት የዳበረ ወጣት ለላቀ የማኅበረሰብ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ የማስ ስፖርት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አካሄዷል።
በመርሃ ግብሩም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ሕይወት ሃይሉ በዚሁ ወቅት የወጣቶች መገንቢያ ማዕከላት ጠንካራ ስብዕና ያላቸውን ወጣቶች በማፍራት ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ በጋራ በሚያከናውነው የማስ ስፖርት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤናው የተጠበቀ ማኅበረሰብ እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር ለእርስ በእርስ ትስስር ከፍያለ አስተዋፅኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።
የወጣት ማዕከላትን በማጠናከር ረገድ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ ባለሃብቶችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በአካል ብቃት እንቅስቃሴው የተሳተፉ ወጣቶች አዕምሮ በእውቀት እንደሚበለጽግ ሁሉ ለአካልና ስብዕና መዳበር ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያስፈልጋል ብለዋል።
የማስ ስፖርት መጠናከር ከሱስ የጸዳና የተሻለ አስተሳሰብ ያለው ማኅበረሰብ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል ወጣቶቹ።
በመሆኑም በስፖርት የተገነባና ብቁ ዜጋ ለማፍራት ማኅበረሰቡ በየአካባቢው ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ልምድ እንዲያደርግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራት እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ 113 የወጣት ማዕከላት ያሉ ሲሆን ጤናማ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ስብዕና ያላቸው ወጣቶችን በማፍራት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው።