ቀጥታ፡

10ኛው የአባይ ናይል ማራቶን ሩጫ በባህርዳር ተካሄደ

ባህር ዳር፣ መጋቢት 5/2013(ኢዜአ) 10ኛው የአባይ ናይል ማራቶን የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድደር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄደ ።

በውድድሩ ታዋቂና ከተለያዩ የአትሌቲክስ ክለቦችና ፕሮጀክቶች የተውጣጡ ከ60 በላይ አትሌቶችን ጨምሮ በርካታ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር የአባይ ናይል ማራቶን ሩጫ ውድድር የከተማውን ዕድገትና ገፅታ የሚቀይር ነው።

ውድድሩ በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶ እንዲወጣና ሀገራቸውን የሚያስጠሩ ተተኪ አትሌቶችን ማፍሪያ እንዲሆን ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ባለሃብቶችና ሌሎች አካላትም ስፖርቱ እንዲያድግና እንዲጎለብት እንዲሁም ከተማው የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የውድድሩ አዘጋጅ አትሌት መልካሙ ተገኝ በበኩሉ ውድደሩ የዛሬ 10 ዓመት መጀመሩን አስታውሷል።

የክልሉን ስፖርት ማደሳገድ፣ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት፣ ህብረተሰቡ ስፖርትን ባህሉ እንዲያደርግና ጤንነቱ እንዲጠብቅ በማሰብ ውድድሩ መጀመሩን አመልክቷል።

ቀደም ሲል የባህርዳር ከተማ ህዝባዊ ሩጫ በሚል ሲጠራ የቆየው ውድድር ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የናይል ማራቶን በሚል ሲካሄድ መቆየቱን ጠቁሟል።

በዘንድሮው ዓመት ደግሞ አባይ ሃብታችን፣ ንብረታችን መሆኑን ለአለም ህብረተሰብ ለማስተዋወቅ የአባይ ናይል ማራቶን በሚል ውድድሩ መካሄዱን አስረድቷል።

በቀጣይ የአባይ ናይል ማራቶን ሩጫ ትልቅ ቦታ እንዲደርስ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን፣ ባለሃብቶች፣ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል ።

ውድድሩን ወደ ግማሽ ማራቶንና 42 ኪሎ ሜትር ለማሳደግ ማሰቡን አመላክቷል።

በውድድሩ ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ የተውጣጡ ከ60 በላይ ታዋቂና በፕሮጀክት የታቀፉ አትሌቶች ጨምሮ በርካታ የባህር ዳር ነዋሪዎች ተሳትፈዋል ።

በውድድሩ በወንዶች 1ኛ የወጣው የመብራት ኃይል አትሌቲክስ ክለብ አትሌት ጊዜአለው አበጀ በውድድሩ ሲሳተፍ የአሁኑ ሶስተኛ ጊዜው መሆኑን ተናግሯል።

የዛሬውን ጨምሮ ለተከታታይ ሁለት ጊዜ ውድድሩን በአንደኝነት እንዳጠናቀቀ ጠቅሶ “ውጤቱ በቀጣይ በርትቼ በመስራት የክለቤንና የሀገሬን ስም እንዳስጠራ ያግዘኛል” ብሏል።

በሴቶች 1ኛ በመሆን ውድድሩን ያጠናቀቀችውና የደባርቅ ዋልያ አትሌቲክስ ክለብ አትሌት ዓለምአዲስ እያዩ በበኩሏ “በማሸነፌ እጅግ ደስተኛ ነኝ” ብላለች።

በውድድሩ ኑሮውን አሜሪካ ያደረገው አትሌት በላይነህ ዲንሳሞና ሌሎች ታዋቂ አትሌቶች ተገኝተው ልምድና ተሞክሯቸውን ለተተኪ አትሌቶች አጋርተዋል።

በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ አትሌቶች የ10 ሺህ፣ የ6ሺህና የ4 ሺህ ብር የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም