ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት የመረዳዳት ባህል እንዲጎለብት ያስችላል - በጎ ፍቃደኞችና ተጠቃሚዎች

ሀምሌ 21/2010 የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ሀገራዊ አንድነት፣ እድገትንና የመረዳዳት ባህልን  እንደሚያጠናክር አስተያየታቸውን የሰጡ በጎ ፍቃደኞችና ተጠቃሚ ተማሪዎች ተናገሩ። በበጎ ፈቃደኝነት መሳተፍ ከጀመረ ሰባት አመታትን ያስቆጠረው  ዳዊት ዳዲ በበጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በላይ ዘለቀ ቁጥር-2 ትምህርት ቤት  ክረምቱን በበጎ ፈቃደኝነት በማስተማር ላይ ነው፡፡ የበጎ ፈቃድ አግልግሎት መስጠት ታዳጊ ህጻናት  ሌሎች ሰዎችን የመርዳዳት ልምድ  እንዲያጎለብቱ ከማስቻሉም በላይ  በህበረተሰብ ዘንድ ሁለንተናዊ መስተጋብር እንዲጠናከር ያስችላልም  ነው ያለው፡፡ በዚሁ ትምህርት ቤት ሌላው በጎ ፍቃደኛ መምህር ነጋሽ ሞገስ  በክረምት ትምርት ቤቶች ስለሚዘጉ ትርፍ ጊዜውን ተማሪዎችን በማገዝ  ለማሳለፍ መምረጡን ይናገራል፡፡ “ተግባር ከቃላት ይበልጣል” ያሉት  መምህሩ ቅን አስተሳሰብ ያለው ዜጋ ማፍራት የሚቻለው ሰርቶ በማሳየት መሆኑን ገልጸው  ከፍለው መማር የማይችሉ ተማሪዎች  ከፍለው ከሚማሩት ጋር መወዳደር እንዲችሉ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው  ወደ ዚህ ተግባረ የገባሁት  ብለዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ  የሚሰጠው ነጻ የበጎ ፈቃድ ትምርት ተጠቃሚ  በመሆኗ መደሰቷን የገለጸችው ተማሪ የትምወርቅ  አየለ  ወደፊት  በትርፍ ጊዜዋ በፍቃደኝነት  ህብረተሰቡን እደሚታገለግል  ትናገራለች። ተማሪ የትምወርቅ ከፍላ መማር የማትችል መሆኗን ገልፃ ይሄን እድል ማግኘቷ  ከፍለው ከሚማሩት ጋር ተወዳዳር እንድሆን ያግዘኛል ብላለች፡፡ ትምህርታችንን  ጠንክረን  ማጥናት እንዳለብንና ወደ  ደፊት ሊያጋጥሙን ስለሚችሉ  ጉዳዮችም ግንዛቤ ይሰጡናል ነው ያለችው፡፡ በተመሳሳይ በሚኒልክ  አንደኛ  ደረጃ  ትምህርት  ቤት  በበጎ ፍቃደኝነት በማስተማር  ተግባር ላይ የተሰማራችው  የሲቪል ኢንጂነሪንግ   ተመራቂ  ሰሚያ ጀማል  ከዚህ  በፊትም  በቀይ መስቀልና  በሌሎችም  ተቋማት  የበጎ ፈቃደኝነት  አግልግሎት  መስጠቷን  ገልፃለች። የአንደኛ ደረጃ  ትምህርት ላይ  እያለች  የበጎ ፍቃደኝነት  አገልግሎት መስጠት  እንደጀመረች የምትናገረው  ሰሚያ  በነዚህ ተግባራት ላይ መሳተፍ  ታዳጊዎች  የመረዳዳትን ባህል እንዲያዳብሩ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያለችው። ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር አብይ አህመድ ወጣቱ  የእረፈት ጊዜውን  በተለያዩ  ተግባራት  በበጎ  ፈቃደኝነት  በመሳተፍ  እንዲያሳልፍ ያስተላልፉት  መልእክት መነቃቃት እንደፈጠረባትም  ነው የተናገረችው፡፡ ሌላዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት  ተሳታፊ  የሁለተኛ አመት  የኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ  ተማሪ ሰለማዊት አሰፋ በጎ ተግባር  ቤተሰብን   ከማገዝ  እንደሚጀምር ገልጻ  ከዚህ በፊትም የዘመድና የጎረቤት ልጆችን  ታስጠና እንደነበር  ተናግራለች። በጎ ፍቃደኝነት ለወደፊት ህይወቷ ልምድ ለመቅሰም እንደሚረዳት  የገለፀችው ተማሪ ሰላማዊት     ሁሉም ወጣቶች  በበጎ ገፈቃደኝነት  ቢሳተፉ  የኢትዮጵያዊነት  መገለጫችን  የሆነው  የመረዳዳት  ባህል ተጠብቆ እንዲቆይ ያስችላል  ነው ያለችው፡፡ በትምህርት ቤቱ  የሚሰጠውን ትምህርት በመከታተል ላይ  ያለችው  የስምንተኛ  ክፍል ተማሪ  ማርታ ታደሰ   የሚሰጣት ትምህርት  በበጋ  ለምትከታተለው  የመደበኛ  ትምርት  ቅድመ  ዝግጅት  እንድታደርግ  የሚያስችላት መሆኑን ተናግራለች። ተማሪ  ማርታ እኛ  ተማሪዎች   የአስተማሪዎችን ፈለግ  በመከተል   ወደ ፊት  ሀገራችንን  በበጎ ፈቃኝነት  ማገልገል ይኖርብናል ብላለች፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም