ቀጥታ፡

የውስጥ ችግሮችን ተነጋግሮ በመፍታትና አንድነትን በማጠናከር የውጭ ጣልቃ ገብነት መከላከል ይቻላል-ምሁራን

የውስጥ ችግሮችን ተነጋግሮ በመፍታትና አንድነትን በማጠናከር የውጭ ጣልቃ ገብነት መከላከል ይቻላል ሲሉ አስታያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ተናገሩ።

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡት የአዲስ አበባ፣ የሀዋሳ እና የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህራን ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮቿን በራሷ የመፍታት አቅም አላት ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር በመሆኗ የውስጥ ችግሮችና ጉዳዮቿን በራሷ የመፍታት መብት እንዳላት የጠቀሱት ምሁራኑ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተሰራው የህግ ማስከበር ስራ የውስጥ ጉዳይ እንጂ አለም አቀፍ ይዘት የለውም ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰርና ተመራማሪ ዶክተር ሰለሞን ለታ፤ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሱ መፍታት የምትችል ሉዓላዊ አገር መሆኗን ተናግረዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሄደበት መንገድ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ምህንድስና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ምህረት ዳናንቶም እንዲሁ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልገው ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንግባ የሚሉ አገራት ከዚህ ቀደም ሶሪያ፣ የመን እና ኢራቅ ገብተው አገራቱ አሁን ላሉበት ውጥንቅጥ እንደዳረጓቸው ተናግረዋል።

በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ አካላት አገራቱን ሲያምሱ እንጂ መፍትሄ ሲያመጡ አልታየም ነው ያሉት።

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያዊያን ያሉብንን ውስጥ ችግሮችን ታነጋግሮ በመፍታት እና አንድነትን በማጠናከር ጣልቃ ገብነትን ልንከላከል ይገባል ብለዋል።

የውስጥ አንድነትን በማጠናከር የውጭ ጣልቃ ገብነትን መከላከል ይቻላል የሚሉት የአምቦ የኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ መምህሩ ዶክተር ብርሃኑ ከበደ ሉዓላዊነት የሚጥስ ጣልቃ ገብነት ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም ይላሉ።

ያሉብንን የፖለቲካና የውስጥ ችግሮች ከፈታንና አንድነታችንን ካጠናከርን የውጭ ጣልቃ ገብነትን መከላከል እንችላለን ሲሉም አክለዋል።

የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ምህንድስና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ምህረት ዳናንቶ የህግ ማስከበር ዘመቻው ሲጀመር እጃቸውን ያላስገቡ አገራት አሁን ጣልቃ ለመግባት ፍላጎት ማሳደራቸው የአገሪቱን አንድነት ለማፍረስ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሰላም የውጪ ጣልቃ ገቦች መተው ከሚሰጡት ሰላም በእጥፉን እንደሚበልጥ ገልፀው  ይሄንን ሰላምና አንድነት ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባነሳው ጉዳይ ላይ ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድ ጣልቃ መግባት ተገቢ አለመሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም