ቀጥታ፡

የአማራ ልማት ማህበር ለኮምቦልቻ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ደሴ ፤ መጋቢት 4/2013 (ኢዜአ) የአማራ ልማት ማህበር /አልማ / በደቡብ ወሎ ዞን ለኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

የማህበሩ የዲያስፖራ በጎ ፍቃደኞችና አጋር አካላት ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጉታ እንደገለጹት፤ ማህበሩ የክልሉን ህዝብ በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡

ለኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል የተደረገው ድጋፍም የማህበሩ አንዱ የስራ አካል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከድጋፉ መካከል የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን፣ የህሙማን ተኝቶ መታከሚያ አልጋ፣  ዊልቸር፣  ለቀዶ ህክምና የሚያገለግሉ፣  አልትራ ሳውንድ ማሽን እና  የደም ናሙና መመርመሪያ ይገኙበታል፡፡

የህክምና ቁሳቁሶቹ   ማህበሩ  ከሮተሪ ክለብ  እንዲሁም ካናዳ የሚኖሩ የክልሉንና ለሌሎች ተወላጆች ጋር በማስተባበር  የተገኘ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ በቀጣይም  ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም  አስረድተዋል፡፡

የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ይመር በበኩላቸው ሆስፒታሉ በ 172 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ጥር 2013 ዓ.ም. ቢመረቅም  በሰው ኃይልና በግብዓት ጉድለት ስራ አለመጀመሩን ገልጸዋል።

ስራውን ለማስጀመር የሚያስችል የ163 የሰው ኃይል ቅጥርና ግብዓት የማሟላት ስራ መጀመሩን ጠቁመው ለዚህም  ከከተማው፣ ዞን ፣ ክልልና ፌደራል የሚመለከታቸው  አካላት  ጋር   በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንተነህ ደመላሽ  ሆስፒታሉን ስራ ለማስጀመር አስተዳደሩ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል፡፡

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር የመድሃኒትና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ እያመቻቹ መሆናቸውን ጠቅሰው እስካሁን ድጋፍ ላደረጉትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም