ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያና ጃፓን አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያና ጃፓን አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ
መጋቢት 4/2013(ኢዜአ) የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያና ከጃፓን አምባሳደሮች ጋር ከሀገራቱ ጋር ስላለው ግንኙነትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጽ/ቤታቸው ተወያዩ።
አቶ ደመቀ ከደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ የኮድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ደቡብ ኮሪያ የቁሳቆሶችን ድጋፍ አንዲሁም የተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ ላበረከተችው አስተዋጽአ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ያላቸውን አድናቆት ገልጸውላቸዋል።
ደቡብ ኮሪያ የምትከተለውን የልማት ሞዴል ኢትዮጵያ የምታደንቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
አምባሳደር ካንግ ሲዮክሂ በበኩላቸው በኮርያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከደቡብ ኮርያ ጎን በመቆም ያደረጉትን አስተዋጽኦ በማስታወስ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በደም የታሳሰረ ታሪካዊ ግንኙነት መሆኑንም አንስተዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት አሁን ካለው የሁለትሽ ትብብር ባሻገር በቴክኖሎጂ ሽግግር እና የልማት ፕሮጀክቶች ትብብር መስክም የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈለግ ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ጋር ባደረጉት ውይይት በሁለቱ አገራት መካከል በትምህርት፣ በመስረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም በተሞክሮ ልውውጥ መስኮች ያለው ትብብር የጊዜው እያደገ የመጣ መምጣቱን በማንሳት፤ለዚህም ያላቸውን አድናቆት ገልጸውላቸዋል።
የጃፓን የልማት ትብብር ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ስለሚያካሄድቸው የልማት ድጋፍ ፕሮግራሞችም አቶ ደመቀ ምስጋና አቅርበዋል።
በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትና የመልሶ ግንባታ ስራዎችን በተመለከተም ለሁለቱ አምባሳደሮች ገለጻ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።