ቀጥታ፡

የቡና አምራችና ላኪነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘታችን ልማቱን ለማስፋፋት አቅም ይፈጥርልናል- ከፊል አርብቶ አደሮች

ጎባ መጋቢት 3/2013 /ኢዜአ/  የቡና አምራችና ላኪነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘታቸው አማራጭ የገበያ እድል በመፍጠር በልማቱ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እድል የሚሰጣቸው መሆኑን በባሌ ዞን የሀረና ወረዳ ከፊል አርብቶ አደሮች ገለጹ፡፡

በባሌ ዞን የሚገኙ ስድስት ቡና አምራች ከፊል አርብቶ አደሮችና አንድ ህብረት ስራ ዩንየን  ለመጀመያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና አምራችነትና ላኪነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል።

የማረጋገጫ ሰርትፍኬት ካገኙ መካከል በዞኑ የሀረና ወረዳ ነዋሪ ከፊል አርብቶ አደር ሃጂ ኡመር ባቲ ለኢዜአ እንደገለጹት ከእንስሳት እርባታ በተጓዳኝ 11 ሄክታር ማሳ ላይ ቡና እያለሙ ነው።

በቡና ልማት የቆያ ልምድ ቢኖራቸውም ለሀገር ወስጥ ገበያ ለሚያቀርቡት የቡና ምርት ተገቢውን ዋጋ ስለማያገኙ የልፋታቸውን ያክል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ተናግረዋል ።

ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በኩል በቅርቡ የቡና አምራችና ላኪነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ሰርተፊኬቱን ማግኘታቸው የሚያመርቱን ቡና ቀጥታ ለውጭ ገበያ በመላክ በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ የሚያስችላቸውን አማራጭ እድል የሚፈጥረላቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

ለቡና ምርታቸው የተሻለ ዋጋ ማግኘታቸው ገቢያቸውን በማሳደግ የቡና ልማቱን ለማስፋፋት የሚያስችል አቅም የሚፈጥርላቸው መሆኑን አመላክተዋል።

"አሁን ላይ በየዓመቱ በአማካኝ የማገኘውን  80 ኩንታል ጥሬ ቡና በቀጥታ ለውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችለኝን የእውቅና ሰርተፊኬት በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ " ያሉት ከፊል አርብቶ አደሩ የቡና ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ለመላክ ከወዲሁ እየተዘጋጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

"ከዚህ በፊት አማራጭ የግብይት ሥርዓት ባለመዘርጋቱና  የአካባቢው  ከፊል አርብቶ አደርም በእድሉ ፈጥኖ ተጠቃሚ ባለመሆኑ እኛ በምናመርተው ቡና ተጠቃሚዎች ደላሎች ነበሩ " ያሉት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ ከፊል አርብቶ አደር ሀሰን ሁሴን ናቸው፡፡ 

የተሰጣቸው የቡና አምራችና ላኪነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ጥራት ያለው ቡና በማምረት በቀጥታ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

ሰርተፊኬቱ የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለገበያ በማቅረብ በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ ስለሚያስችላቸው በቡና ልማትና ንግድ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እድል የሚፈጥረላቸው መሆኑን አመላክተዋል ።

ከምርት ጀምሮ በምርት ስብሰባ፣ ዝግጅት፣ ክምችት፣ ማሸግና ለገበያ እስከማቅረብ ባለው ሂደት የተፈቀደ የአሠራር ሥርዓት በመከተል የተፈጥሮ ባህሪና ጣዕም የጠበቀ ቡና  ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ከፊል አርብቶ አደሮቹ  አስታውቀዋል ።

ከፊል አርብቶ አደሮቹ ባገኙት የላኪነት ሰርተፍኬት ተጠቅመው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ አሜሪካ ፣ጀርመንና አውስትራሊያ ለሚገኙ ኩባንያዎች ናሙና ተልኮ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በፋርም አፍሪካ ድርጅት የባሌ ኢኮ- ሪጂን ሬድ ፕላስ ፕሮጄክት አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ገዛኽኝ ናቸው፡፡

ለውጭ ሀገራት ኩባንያ የተላከው ናሙና ተቀባይነት ሲያገኝ በአርብቶ አደሮቹ የተመረተ 37 ሺህ 590 ኪሎ ግራም ቀሽር ቡና ለመላክ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ  አርሶ አደሮቹ ያገኙት የላኪነት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ጥራት ያለው ቡና በማምረት የዓለም ገበያ አማራጮችን ለመዳሰስ ትልቅ እድል ይፈጥራል ፡፡

በዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የቡና ጥራትና ቅመማ ቅመም ቡድን መሪ አቶ ወንድወሰን ነጋ  በዞኑ በሀረናና ደሎ መና ወረዳዎች  በቡና ልማት ግንባር ቀደም የሆኑ ስድስት ከፊል አርብቶ አደሮችና አንድ ዩንየን ጥሬ ቡናን ለውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችላቸውን ሰርተፍኬት አግኝተዋል፡፡

ቡድን መሪው እንዳሉት ከገበያ እጦት የተነሳ በዞኑ በየዓመቱ በአማካይ ከሚመረተው 15 ሺህ ቶን ጥሬ የቡና ምርት ውስጥ 700 ቶን የሚሆነው ብቻ ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል፡፡

የላኪነት ሰርተፊኬቱ የቡና ጥራትና መጠን በማሳደግ ለማዕከላዊና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚያችል እድል የሚፈጥር መሆኑን ቡድን መሪው አስታውቀዋል።

በባሌ ዞን ከ51 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ ሲሆን ከሚለማው ውስጥ 26 በመቶ የሚሆነው የተፈጥሮ ጫካ ቡና መሆኑን ከዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሀገሪቱ የቡና ግብይትን ዘመናዊነት፣ ህጋዊነትና ፍትሃዊነት በማሻሻል የቡና አምራቾች፣ የግብይት ተዋንያንና የሀገሪቱን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል የተለያየ አማራጭ ያለው የግብይት ሥርዓት መዘርጋት አማራጭ የሌለ ጉዳይ ነው።

በዚሁ መሰረት የቡና ግብይት እና ጥራት ቁጥጥር አዋጅ 1051/2009 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ እየተሰራበት መሆኑን የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም