ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት ነገ በድሬዳዋ ይጀመራል

34

ድሬዳዋ፤ መጋቢት 3/2013 (ኢዜአ) ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት ነገ በድሬዳዋ አስተዳደር ለሚገኙ ጤና ባለሙያዎች መሰጠት እንደሚጀምር የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚደርሰው የኮቪድ ቫይረስ መከላከያ ክትባት ውስጥ 6ሺህ ለድሬዳዋ የተሰጠ ኮታ ነው፡፡

የመከላከያ ክትባቱ ለቫይረስ ግንባር ቀደም ተጋላጭ ለሆኑት በመንግስትና ግል ጤና ተቋማት ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ይሰጣል ብለዋል፡፡

ነገ የመጀመሪያው ዙር ክትባት የሚወስዱ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ሁለተኛውን ዙር ደግሞ ከ8 እስከ 12 ሣምንት ውስጥ እንደሚሰጣቸው  ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ዙር የሚወስደው ክትባት እስከ 90 በመቶ ብቻ ቫይረሱን የመከላከል አቅም የሚኖረው በመሆኑ በሽታውን የመከላከያ መንገዶች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ ፤ በቀጣይ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸውን ሰዎች እንዲሁም አዛውንቶችና የፀጥታ አካላት ክትባቱን የሚያገኙበት መንገድ ማመቻቸቱ ይቀጥላል፡፡

ህብረተሰቡ ከኮሮና  ራሱን እንዲጠብቅ ከማስተማሩ በተጓዳኝ የቫይረሱን መከላከያ ፕሮቶኮሉን በማያከብሩ ላይ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል፡፡

በህብረተሰቡ መዘናጋት ምክንያት በኮሮና ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን ያመለከቱት የጤና ቢሮው ኃላፊዋ፤ አሁን ባለው የስርጭት መጠን ማሻቀብ የድሬዳዋ እንቅስቃሴ ሊዘጋ ይገባ ነበር፤ ነገር ግን ካለው የኑሮና የኢኮኖሚ ዝቅተኛነት ነው ክፍት የተደረገው ብለዋል፡፡ 

በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለት ነጥብ ሁለት  ሚሊዮን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት መመቻቸቱን ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም