ከተማ አቀፉ የሴቶች ስፖርት ውድድር ነገ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
ከተማ አቀፉ የሴቶች ስፖርት ውድድር ነገ ይጀመራል

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2013 10ኛው ከተማ አቀፍ የሴቶች ስፖርት ውድድር ነገ እንደሚጀመር የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።
ውድድሩ "የሴቶች ተሳትፎ ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ ከመጋቢት 4 እስከ 12 ቀን 2013 እንደሚካሄድ ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኮሚሽነር ዳዊት ትርፉ ውድድሩ ሴቶች በስፖርት መስክ በስፋት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚካሄድ ነው ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የሴቶች ስፖርት ውድድር ከተማ አስተዳደሩን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥም ያግዛል።
በስምንት የውድድር ስፖርቶችና በ4 የፌስቲቫል ውድድሮች በድምሩ 4 ሺህ ሴቶችን ለማሳተፍ የታቀደ ሲሆን ከከተማዋ 11 ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ቡድኖች ተሳታፊ ይሆናሉ።
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽንና የሴቶች ስፖርት ኮሚቴ በጋራ ያዘጋጁት የዚህ ውድድር አስተናጋጅ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መሆኑን አቶ ዳዊት ገልፀዋል።
በውድድሩ እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቮሊቦል፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ዳርት፣ ቼዝ፣ ፓራኦሊምፒክ፣ መስማት የተሳናቸው ውድድርና የባህል ስፖርቶች ተካተዋል።
እንደ ገመድ ጉተታ፣ እንቁላል በማንኪያ ይዞ መሮጥና የጆንያ ውስጥ ሩጫ ያሉ አዝናኝ ስፖርቶችም ይካሄዳሉ።
የከተማ አቀፍ የሴቶች ስፖርት ውድድር በየሁለት ዓመቱ የሚከናወን ሲሆን 9ኛው ውድድር በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተናጋጅነት ነው የተካሄደው።