በትግራይ ክልል የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እና የመብት ጥሰት እንዲጣራ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነች … አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እና የመብት ጥሰት እንዲጣራ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነች … አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ
መጋቢት 3/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እና የመብት ጥስት እንዲጣራ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንበተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ አስታወቁ።
ሀገሪቱ የገጠማትን ቀውስ ለመፍታት ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።
አምባሳደሩ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ትግራይ ክልልን መልሶ ለመገልባትና እየተሰጠ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ አስመልክተው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በፊት ከገጠሙት ሀገራዊ ፈተናዎች ሁሉ የአሁኑ የተለየ የሚያደርገው የህወሀት የጥፋት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የከፈተው ጥቃት ሀገርን ለማፈራረስ አላማን አንግቦ መነሳቱ ነው ብሏል።
የጥፋት ቡድኑ በፈጠረው የጸጥታ ችግር በክልሉ መሰረተ ልማትን ከማውደሙም ባለፈ የሰው ህይወት መጥፋቱና በርካታ ሰዎች መሰደዳቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በትግራይ ክልልና አጎራባች ክልሎች የተፈጠረው የጸጥታ ስጋት ዜጎችን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማጋለጡን የጠቀሱት አምባሳደር ታዬ፤ የትግራይ ክልል ቀድሞውንም 1.7 ሚሊዮን ዜጎች የሴፍቲኔት ተጠቃሚ በመሆናቸው ችግሩን አባብሶታል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የአየር ጸባይ ለውጥና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ፍትሃዊ አለመሆን ለድህነትቱ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፤ ችግሮቹን ለመፍታት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ፖሊሲ ቀርጻ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከአለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በትብብር መስራቷንም አውስተዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እና የመብት ጥስት እንዲጣራም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ጠቅሰዋል።
በቅርቡም የክልሉን የሰብአዊ ድጋፉ ሂደት የአለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዳቪድ ባስሬይ እና የአለማቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ መልካም መሆኑን ክልሉን በጎበኙበት ወቅት መናገራቸውን አምባሳደሩ በደብዳቤአቸው ጠቅሰዋል፡፡