የኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ የቆየ የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱ ተገለጸ
መጋቢት 3/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ የቆየ እና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት በልዩ ልዩ መስክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን መምጣቱ ተገልጿል።
በዩጋንዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አለምጸሀይ መሰረት ከዩጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳም ኩቴሳ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮችና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያዩ።
በውይይቱም ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ የቆየ እና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተገለጸ ሲሆን ግንኙነቱም በልዩ ልዩ መስክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን ተጠቅሷል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጠናዊ ሁኔታ ላይ በተካሄደው ውይይት በተለይም መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን የመልሶ ግንባታ እና ሰብዓዊ እርዳታ ስራዎችን አስመልክተው አምባሳደር አለምፀሀይ መሰረት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መንግስት ክልሉንም ለአለምአቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች እና ለአለምአቀፍ ሚዲያዎች ያለ ገደብ ክፍት ማድረጉን፣ የአለምአቀፍ ማህበረሰቡና እርዳታ ሰጪዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን እና መሬት ላይ ያለው ሀቅና በተወሰኑ የሚዲያ አካላት የሚነዛው የተሳሳተ ትርክት የተለያየ እንደሆነም አምባሳደሯ አስረድተዋል፡፡
ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት በሀይል እንደያዘችና ይህም የሁለቱን ህዝቦች የቆየ ግንኙነት እንደማይወክልም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ጥረት በማስረዳት፤ ኢትዮጵያ ውይይት ከመጀመሩ በፊት ሱዳን የያዘችውን መሬት በአስቸኳይ ለቃ እንድትወጣ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧን ገልጸዋል።
ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን መፍትሄ በሚል ሶስቱ ሀገራት ጉዳዩን በአፍሪካ ህብረት አጋዥነት መፍታት የሚያስችል አቅም አለ ብላ እንደምታምንም እንዲሁ።
የዩጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳም ኩቴሳ በበኩላቸው አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት ተቀራርበው መስራት እንደሚገባቸውና ሁለቱ አገራት የድንበር ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለቀጠናው ሰላም አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው የመከሩት።
የናይል ወንዝን በተፋሰሱ ሀገራት ያለው ችግር የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት እንጂ የውሃ እጥረት አለመሆኑን ጠቅሰው ሊከሰት የሚችል የውሃ እጥረትን አስቀድሞ ለመከላከል ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በመወያየት የውሃ ሀብት ልማት ስራዎች ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።