የኢትዮጵያ መንግስት ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር የአውሮፓ ህብረት ያበረታታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር የአውሮፓ ህብረት ያበረታታል
መጋቢት 3/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት በአካባቢው መረጋጋት እና ሰላም ለማስጠበቅ ለሚያደርገው ጥረት ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር የአውሮፓ ህብረት እንደሚያበረታታ ገለጸ።
የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለመቅረፍ ለሚያደርገው ስራ እውቅና ይሰጣል።
ህብረቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ለሰላምና መረጋጋት ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና የምታደርገውን ዘርፈ ብዙ ሚና ይገነዘባል ነው ያለው በመግለጫው፡፡
የአውሮፓ ህብረት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ያለ ችግር እንዲቀጥል ፊላጎት እንዳለው ገልጾ፤ ህብረቱ በትግራይ ክልል ለሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ከተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ሙሉ ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቋል።
በዚህ መሰረት ሰላማዊ እና የተቀናጁ ውሳኔዎችን ለመውሰድ የአውሮፓ ህብረት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ውይይቶችን ለማድረግ እንደሚፈልግም ገልጿል።
ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ዴሞክራሳያዊ የሽግግር ሂደት ላይ መሆኗን ገልጾ ፤ በርካታ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ተተግብረዋል ነው ያለው ህብረቱ በመግለጫው፡፡
በመጨረሻም በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ተአማኒ እና ግልፅ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት የአውሮፓ ህብረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።