ኢትዮጵያውያን በኒውዮርክ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጽ/ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በኒውዮርክ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጽ/ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ
መጋቢት 03/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኒውዮርክ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጽህፈትቤትን ጨምሮ በሲኤን ኤን ፤ኒውዮርክ ታይምስ እና በተለያዩ ቦታዎች ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል።
ሰልፈኞቹም የመንግስታቱ ድርጅትና ሌሎችም አካላት በጽንፈኛው የህወሃት ደጋፊዎች የሚሰራጨውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ተመርኩዘው በኢትዮጵያ ላይ ለመፍጠር እየሞከሩ ያሉትን ያልተገባና ኢፍትሃዊ ጫና እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ሲ ኤን ኤን እና ሌሎች የሚዲያ ተቋማትም ያልተጨበጠ መረጃን ተንተርሰው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጻረርና ከእውነት የራቁ መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲታቀቡ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን የህግ የማስከበር እርምጃ እንዲሁም በትግራይና በሌሎች አካባቢዎች እያደረገ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታና የመልሶ ማቋቋም እርምጃ እንደሚደግፉ ሰልፈኞቹ ገልጸዋል።
አሜሪካ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር በፍትሃዊነት እንዲቋጭ እና ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ለቃ እንደትወጣ አዎንታዊ ሚና እንድትጫወት ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የሃሰት መረጃ ስርጭትን በማምከን ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ልማትና ሰላም ያላቸውን ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሰልፈኞቹ አረጋግጠዋል።