ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ጂቡቲ በጸጥታ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

መጋቢት 03/ 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በጸጥታ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

የሁለቱ ሀገራት ስምምነት የጋራ የፀጥታ ሥጋቶችን በብቃት ለመመለስ ፣ የድንበር ደህንነት ዝግጁነትን ለማጎልበት እንዲሁም ብቁ የፖሊስ ሠራተኞችን ለማፍራት አላማ ያደረገ ነው።

የመግባቢያ ሰነዱ የተፈረመው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ፣ የጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዲላሂ አብዲ ፣ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እንዲሁም በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ዲፕሎማቶች በተገኙበት ነው፡፡

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ እንደተናገሩት በደህንነትና በፖሊሳዊ ዘርፎች የጋራ ጥረቶችን በማሳደግ ሁለቱ ወንድማማች አገራት በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም በቀጣይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የመግባቢያ ሰነዱን ለመፈረም ከአሁኑ የተሻለ ጊዜ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲ በበኩላቸው የመግባቢያ ስምምነቱን ወደ ተግባር መለወጥ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በቀጣይም በሁለቱ ሃገራት መካከል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በየስድስት ወሩ እየተገናኙ ምክክር ለማድረግም ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በሰላም ማስከበር ፣ በፎረንሲክ ሳይንስ ፣ በሰው ኃይል፣ በትምህርት እና ሥልጠና ላይ ሁለቱ ወገኖች በትብብር ለመስራት መስማማታቸውም ተመልክቷል፡፡

በድሬዳዋ እና በጅቡቲ የጋራ ግብረ ኃይል ለማቋቋምም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም