ሠብዓዊነት እና ፍቅር ለትግራይ እና መተከል የመጀመሪያውን ዙር ድጋፍ አሰራጨ - ኢዜአ አማርኛ
ሠብዓዊነት እና ፍቅር ለትግራይ እና መተከል የመጀመሪያውን ዙር ድጋፍ አሰራጨ
መጋቢት 2/2013(ኢዜአ) ሠብዓዊነት እና ፍቅር ለትግራይ እና መተከል ጥምረት የመጀመሪያውን ዙር ድጋፍ ወደ ጋሌሳና መቀሌ ዛሬ አሰራጭቷል።
የጥምረቱ ሃሳብ አመንጪና ሰብሳቢ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ "ዛሬም የሁሉም ኢትዮጵያዊ የመተሳሰብ መንፈስ እንዳለ አይተናል" ብሏል።
የጥምረቱ ዓላማ በአካባቢዎቹ ያለውን ችግር በአንድ ጊዜ ለመፍታት ሳይሆን ዜጎች እንደዜጋ ሀላፊነት ወስደው የወገናቸው እንባ የእኔም ብለው የሚያጽናና ተስፋ ለመስጠት መሆኑን ገልጿል።
በዚሁ መሰረት "ከአገር ውስጥና ከውጭ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚችለውን ሁሉ አድርጎልናል" ያለው ታማኝ በተደረገው ርብርብ በአገር ውስጥ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል ብሏል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ተወካይ አቶ ዳንኤል አየለ በበኩላቸው ግሎባል አሊያንስ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚጋጥሙ ችግሮች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል።
የተሰባሰበው ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ ቀይ መስቀል የሂሳብ ቁጥር ገቢ መደረጉንም አክለዋል።
የአሰራር ስርዓትና ደንቡን በመከተል 1 ሺህ ኩንታል ዱቄት እና 6 ሺህ 400 ሊትር ዘይት መገዛቱንና ዛሬ ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በተሰጡ ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ እና ወደ ጋሌሶ ለእያንዳንዳቸው 500 ኩንታል ዱቄት መላኩን አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ ወደሁለቱም አካባቢዎች ለእያንዳንዳቸው 3 ሺህ 200 ሊትር ዘይት ተልኳል ብለዋል።
የመተከልና የትግራይ በጎ ፈቃደኛ አሰባሳቢ ወጣቶች በበኩላቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡