ቀጥታ፡

ጃፓን የሱናሚ አደጋ በደረሰባት ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቀረበች

መጋቢት 2 ቀን 2013 (ኢዜአ) ጃፓን እ.አ.አ 2011 ደርሶባት በነበረው የሱናሚ አደጋ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቀረበች።

አገሪቱ በኢትዮጵያ የምታደርገውን ሠብዓዊና ሌሎች ድጋፎች አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስታውቃለች። 

የኢትዮ-ጃፓን የወዳጅነት ኮሚቴን የወከሉት በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደሯ ጃፓን ጃፓን እ.አ.አ 2011 የደረሰባት የሱናሚ አደጋ 10ኛ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታሰበ መሆኑን ገልፀዋል።

ጃፓን ደርሶባት ለነበረው የሱናሚ አደጋ ኢትዮጵያ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጓን ያስታወሱት አምባሳደሯ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግር ለመወጣት ከውጭ ከሚደረገው ድጋፍ ጎን ለጎን እርስ በርስ መረዳዳት እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለይ በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል ሠብዓዊ እርዳታ ለማድረስ መንግስት በራሱ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ቢሆንም አሁንም ብዙ ስራ እንደሚያስፈልግ መገንዘባቸውን አስረድተዋል።

"ጃፓን በኢትዮጵያ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሠብዓዊ ድጋፍ እንደምታደርግ አሳውቃለች" ያሉት አምባሳደሯ፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ ሠብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች በመደገፍ ረገድ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀል ገልጸዋል።

አምባሳደሯ የሚደረገውን ሠብዓዊ ድጋፍና ተያያዥ ተግባራትን አስመልክቶ ሠላም ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች አካላት በዋናነት ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያንን ለመመለስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን መገንዘባቸውን ጠቁመዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ጃፓንና ኢትዮጵያ በጥሩ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ችግሮች በሚገጥሟቸው ወቅት በጋራ እንደሚቆሙ ተናግረዋል።

ጃፓን በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ በደረሰው ቀውስ ሠብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ በኩል ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የገጠሟትን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ለማለፍ ጥረት እያደረገች እንደሆነም ዶክተር ነገሪ ለአምባሳደሯ ገልፀውላቸዋል።

በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በተወሰኑ ቡድኖች አማካኝነት ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም መንግስት ሕግ የማስከበር ተግባራትን በማከናወን ውጤታማ እንደሆነ ተናግረዋል።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት መንግስት ያካሔደው ሕግ የማስከበር ተግባር የማይጥማቸውና በህወሓት ቡድን የሚደገፉ አካላት ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሐሰት መረጃዎችን እያሰራጩ እንደሆነም አብራርተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም