ቀጥታ፡

በውሻ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል-የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ባህር ዳር ፤ መጋቢት 2/2013(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በእብድ ውሻ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ  መምጣቱን የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በክልሉ የውሻ በሽታ ያለበትን ደረጃ የሚያሳይና መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የኢንስቲትዩቱ  የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ሰጭና መልሶ መቋቋም ባለሙያ አቶ ሀይሉ አያሌው ባቀረቡት ጽሁፍ እንደገለጹት የውሻ በሽታ   ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ "ራቢስ" ከተባለ  አደገኛ ቫይረስ  የሚመጣ  ነው።

በክልሉ ዘንድሮ ብቻ በበሽታው ታመው ወደ ጤና ተቋማት በመምጣት ህክምናውን ያገኙ ሦስት ሺህ 487 ሰዎች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ፈጥነው ወደ ህክምና ባለመምጣታቸውም በበሽታው ምክንያት የ17 ሰዎች ህይወት ማለፉን አውስተው ፤በርካቶች ወደጤና ተቋማት ሳይመጡ የተጎዱ ሊኖሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

በአብዛኛው በሽታውን በመሸከም ከሚታወቁት መካከል ውሻ፣ ቀበሮ፣ የሌሊት ወፍ፣ ድመትና ሽልምጥማጥ የሚተላለፍ ቢሆንም 99 በመቶ የሚሆነው ወደ ሰው የሚተላለፈው በእብድ ውሻ አማካኝነት እንደሆነ ባለሙያው አስታውቀዋል።

በበሽታው የተያዘ ውሻ ቁጡነትና ፍርሃት፣ ልሃጭ ማዝረብረብ፣ ለመዋጥ መቸገር  የመሳሰሉ  ምልክቶችን ያሳያል ብለዋል።

በሽታውን ለመከላከል ዓይነተኛ መፍትሄው ውሻን  ማሳከም ቢሆንም በኢትዮጵያ የውሻ ባለቤቶች አያያዝ አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ ሊኖር ባለመቻሉ ችግሩ አሳሳቢ እንዳደረገው አስረድተዋል።

ባለሙያው ችግሩን ለመከላከል መንግስት ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖረው፤ የውሻ ባለቤቶች ለራሳቸው ቤተሰብም ሆነ ለሌላው ሲሉ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በባህር ዳር ከተማ የእንስሳት በሽታ ቅኝት ላብራቶሪ የእንስሳት ሃኪም ዶክተር አልማዝ ሀብታሙ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ውሻን የማስከተብ ልማዱ   እየተሸሻለ ቢሆንም  እንደሚቀረው ተናግረዋል።

በከተማዋ ዘንድሮ ከ500 በላይ ውሾች መከተባቸውን ጠቅሰው፤ ሊኖር ከሚችለው የውሻ ብዛት አኳያ በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ውሾችን በየአካባቢው ወደ ሚገኝ የእንስሳት ጤና ጣቢያ ይዞ በመሄደ ህዝባዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ዶክተር አልማዝ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ በውሻ በሽታ  መስፋፋት በአለም ላይ ካሉ ሀገራት በቀዳሚነት የምትሰለፍ መሆኗን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትተዩት ተመራማሪ ዶክተር ባየ አሸናፊ ናቸው።

ይህም በሀገሪቱ ህብረተሰቡ ጤና ላይ አደገኛ የጤና ስጋት የፈጠረ በሽታ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ ሀገር የችግሩን ስፋት ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሽታው አስከፊና በተለይ ህጻናት ከውሾች ጋር ባላቸው ቅርርብ የተነሳ በስፋት ተጎጆች ስለሆኑ ህብረተሰቡ ውሾቹን በአግባቡ በማስከተብ ሊጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ባለቤት አልባ ውሾችን የክትባት ሥርዓት አዘጋጅቶ ማስከተብ ፤  ካልሆነ ደግሞ በአግባቡ የሚወገዱበት አሳራር ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል።

ችግሩ ከዚህ በባሰ የከፋ እንዳይሆንም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጠናከር መልዕክት አስተላልፈዋል።

በውይይት መድረኩ የፌደራል፣ ክልል፣ ዞንና ወረዳ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም