በኢትዮጵያ የግል ባለሃብቱ የነቃ ተሳትፎ የውስጥ አቅምን በማጎልበት ቀጠናዊ ትስስርን ለመፍጠር ያግዛል - አቶ ዑመር ሁሴን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የግል ባለሃብቱ የነቃ ተሳትፎ የውስጥ አቅምን በማጎልበት ቀጠናዊ ትስስርን ለመፍጠር ያግዛል - አቶ ዑመር ሁሴን
አዲስ አበባ ፣መጋቢት 02/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የግል ባለሃብቱ የነቃ ተሳትፎ የውስጥ አቅምን በማጎልበት ቀጠናዊ ትስስርን ለመፍጠር እንደሚያግዝ የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን ገለጹ።
የግብርና ሚኒስቴር የበረሃ አንበጣና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት የሚገዛቸውን አውሮፕላኖች የግዥ ሂደትና ከተገዙ በኋላ የማስተዳደሩን ስራ እንዲረከብለት ከኢትዮጵያው ብሄራዊ አየር መንገድ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ ወደተለያዩ አገራት የሚጓጓዙትን እንስሳት ለማስቀረት ከሳዑዲ ዓረቢያው ሞሀመድ ሃሚድ ኢሊይሳ ኢ.ኤስ.ቲ ድርጅት ጋር የሚሌን የእንስሳት ማቆያ የአስተዳደር ስራውን ለመረከብ ተስማምተዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያን የበረሀ አንበጣና ሌሎች አደጋዎች ሲያጋጥሟት አደጋውን ለመከላከል ወደ ሌሎች አገሮች እንድታማትር ትገደዳለች ብለዋል።
ከተለያዩ አገሮች በኪራይም ሆነ በድጋፍ የሚመጡ አውሮፕላኖች ከፍተኛ ወጪ ከመጠየቃቸው ባሻገር በሚፈለገው ጊዜ እንደማይደርሱ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 20 ወራት አንበጣን ለመከላከል ብቻ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጭ አድርጋለች ይሄም ሆኖ ከቅድመ ምርት ስብሰባና ከዚያ በኋላ ባለው ሂደት የአርሶ አደሩ ሲሶ ምርት ከብክነት እንዳልዳነም አቶ ዑመር አስታውሰዋል።
በመሆኑም መንግሥት ሁሉንም ሥራዎች ብቻውን መስራት ስለማይችል የግል ባለሃብቱን እውቀትና የቴክኖሎጂ አቅም ተጠቅሞ ግብርናውን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ከተለያዩ ዘርፎች በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ኢትዮጵያ በአፋር ክልል በ120 ሚሊዮን ብር የተገነባው የሚሌ የእንስሳት ማቆያ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በዓመት እስከ 400 ሺህ እንስሳትን በማቆየት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ቢችልም፤ እስካሁን ማድረግ የቻለው 60 ሺህ እንስሳትን ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።
እነዚህም ጅቡቲ የእንስሳት ማቆያ ማዕከል ለሁለተኛ ጊዜ ቀርበው ደረጃ ከወጣላቸው በኋላ ወደ ገበያው እየተላኩ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብቷ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንድትችል ሞሀመድ ሃሚድ ኢሊይሳ ኢ.ኤስ.ቲ የተባለ ድርጅት የማቆያ ጣቢያውን እንዲያስተዳደር ለ10 ዓመት ስምምነት መፈራሙን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያው ብሄራዊ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካፒቴን አበራ ለሚ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት የግል ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም መንግሥት የሰጠንን የማስተዳደርና ሥራን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ዜጎች የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ሚናችንን እንወጣለን ብለዋል።
የሳዑዲ ዓረቢያው ሞሀመድ ሃሚድ ኢሊይሳ ኢ.ኤስ.ቲ ድርጅት ተወካይ ሱልጣን ዳድሂ ድርጅታቸው በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ከጣቢያው ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ጥራት ያላቸው እንስሳትን ለማቅረብ እንደሚሰራ ተናግረዋል።