ኮሚሽኑ ከኢትዮጵ ያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር ለመስራት ተስማማ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ከኢትዮጵ ያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር ለመስራት ተስማማ

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 02/2013 (ኢዜአ) የአስተዳደርና ወሰን ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በፖሊሲ፣ በጥናትና ምርምር ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱ ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ዓላማ መሰረት በማድረግ የማንነት ጉዳዮች፣ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የወሰንና በተለይም የፖሊሲ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሥራዎችን በጥናትና ምርምር በመደገፍ በጋራ መስራት የሚያስችል ነው ተብሏል።
የአስተዳደርና ወሰን ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር ዶክተር ጣሰው ገብሬ የፖሊሲና የሕግ ጥያቄዎችን እንዲሁም አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን በተመለከተ ከኢንስቲትዩቱ ጋር ለመስራት ስምምነቱ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በጥናትና ምርምር ክፍተቶችን በመለየት መሻሻል ያለባቸውን ተግባራት በማሻሻል እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የማንነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና የወሰን ጉዳዮችን የተመለከቱ ችግሮችን በመለየትና የፖሊሲ አማራጮችን በማቅረብ ለኮሚሽኑ አስተዋጽኦ መጎልበት የበኩሉን እንደሚወጣም እንጠብቃለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌም በአገሪቷ በተለያዩ ጊዜያት ውዝግቦች የሚነሱበት ሁኔታ መስተዋሉን አንስተዋል።
ይህም በኢኮኖሚ፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎች ዘርፎች አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን ገልፀው ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት በምርምር ላይ የተደገፈ ሥራ መስራት አንዱ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።
"ጉዳዩ ፈታኝና ብዙ ተመራማሪዎች የማይደፍሩት፤ የፖለቲካ አመራሮችም የሚገፉት ሆኖ ቆይቷል" ያሉት ዶክተር መኩሪያ፤ ለመፍትሄው መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በጥናትና ምርምር በመደገፍ የፖሊሲ ንድፈ ሃሳብ ለማቅረብ በርካታ ተመራማሪዎች እንዳሉት ጠቁመው በዚህ ረገድ ለኮሚሽኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የማበርከት ሚና ይኖረዋል ብለዋል።