ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎች ምዝገባ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎች ምዝገባ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2/2013 ( ኢዜአ) ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎች ምዝገባ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ የምርጫ ምልክት ካስገቡ ፓርቲዎች በድምሩ ስምንት ሺህ 209 እጩ ተወዳዳሪዎችን መመዝገቡን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የእጩዎች ምርጫ ሂደትን አስመልክቶ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባን በሁለት ዙር ያካሄደ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ከየካቲት 8 እስከ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረሪ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ከፊል ኦሮሚያ ምዝገባ መካሄዱን አመልክቷል።
ከየካቲት 15 እስከ 26 ድረስ በተከሄደው ሁለተኛ ዙር ምዝገባ ደግሞ በአማራ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ምዝገባው መካሄዱን ነው ሰብሳቢዋ ያስታወቁት።
በአሁኑ ወቅት የእጩዎች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የገለጹት ወይዘሪት ብርቱካን፣ ለ22 ቀናት በተካሄደው የእጩ ምዝገባ ሂደት 8 ሺህ 209 እጩዎች መመዝገባቸውን አክለዋል።
የተመዘገቡት እጩዎች የምርጫ ምልክት ካስገቡ 49 ፓርቲዎች ውስጥ በ47ቱ ያሉ እጩ ተወዳዳሪ መሆናቸውም በመግለጫው ተመላክቷል።
"በምዝገባ ሂደቱ ከሎጅስቲክ ጋር በተያያዘ ችግሮች አጋጥመው ነበር" ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን፤ የትራንስፖርት፣ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ቢሮዎችን ቶሎ አለማዘጋጀትና የጸጥታ ችግሮች የነበሩባቸው ቦታዎች መዘግየት እንዳጋጠመ አስረድተዋል።
በምዝገባ ሂደቱ ፓርቲዎች የተለያዩ ቅሬታዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰው፣ ቦርዱ ከፓርቲዎች የሚቀርበውን አቤቱታ ለመፍታት የሚያስችል ዴስክ አቋቋሞ በፍጥነት ችግሮች እንዲፈቱ ማድረጉን ገልጸዋል።
"እንደ ምሳሌም ሦስት ቦታዎች ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እንደታሰሩ ለቦርዱ ሪፖርት ቀርቦ ነበር" ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን፣ ቦርዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ ማድረጉን ተናግረዋል።
"በምዝገባ ሂደቱ አቤቱታ ያቀረቡ ፓርቲዎች ሁሉም ጥያቄያቸው እንዲመለስ ተደርጓል" ሲሉም ተናግረዋል።
ቦርዱ በምዝገባ ሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የምዝገባ ጊዜው እንዲራዘም ማድረጉን ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፣ በምርጫ አስፈጻሚዎች በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን አመልክተዋል።