የህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት ማጠናቀቁ ለሶስትዮሽ ድርድሩ መሳካት ወሳኝ ነው- ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት ማጠናቀቁ ለሶስትዮሽ ድርድሩ መሳካት ወሳኝ ነው- ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ
ሆሳዕና መጋቢት 2/2013(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጨማሪ ጉልበት ተጠቅሞ በፍጥነት ማጠናቀቁ ለሶስትዮሽ ድርድሩ መሳካት ወሳኝ በመሆኑ የህብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፕሮፌሰር ያዕቆም አርሳኖ ተናገሩ።
ፕሮፌሰሩ ለዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎች ስለ ግድቡ አስተዋጽኦና እየተደረገ ስላለው ድርድር ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ምሁርና ግድብ ዙሪያ ተደራዳሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የሶስትዮሽ ድርድሩ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት በሚያረጋገጥ መልኩ ነው፡፡
ግድቡ ለሀገሪቱ ወሳኝ ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ያዕቆብ የግንባታው በፍጥነት መጠናቀቅ ለድርድሩ ወሳኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ ተገቢውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
ይህም ለኢትዮጵያ ታዳሽ የሆነ ከፍተኛ የሀይል ምንጭ፣ ለህብረተሰብ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት መሻሻል ብሎም ሀገሪቱን ለማዘመን ወሳኝና ጠቃሚ ግድብ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ግድቡ ለሀገሪቱ እድገት ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን ተጨማሪ አቅምና ጉልበት በመጠቀም ግንባታው እንዲፈጸም ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ይህም ሆኖ የግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ እንደሚደርስ ምንም እንደሚያጠራጥር ፕሮፌሰር ያዕቆብ አስታውቀዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የምርምና ማህረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምከትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጸደቀ ላምቦሬ በበኩላቸው፤ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ግድቡ ተጠናቆ ለተፈለገው ዓላማ በሚውልበት ወቅት ያለውን አስተዋጽኦና ስለድርድሩ ግንዛቤ እንዲያዝ የሰጡት ማብራሪያ የተቋሙ መምህራንና ተማሪዎች ጥናትና ምርምር ለማድረግ መነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ግድቡ እንዲጎለብት ከማድረግ አንጻር በአካባቢው የሚገኙ ምንጮችን ከማልማት ባሻገር በሀገር ደረጃ የጮቄን ተራራ ለማልማት በተቋቋመው ፎረም የበኩሉን ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
በድርድሩ በግብጽና ሱዳን የሚስተዋለው አቋም ሀገሪቱ ያላትን ተፈጥሮዊ ሀብት የመጠቀም መብቷን የሚጋፋ በመሆኑ ግድቡን ለመፈጸም ግንባታው በልዩ ትኩረት መቀጠሉ ተገቢ መሆን ገልጸዋል፡፡
የግብጽ አቋም ከጋራ ተጠቃሚነት ይልቅ የራሷን ፍላጎት ብቻ በማንጸባረቅ አለም አቀፍ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚዋዥቅ ሀሳብና አቤቱታ በማቅረብ ወዲህና ወዲያ ማለቷ የሶስትዮሽ ድርድሩ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተመስገን ቶማስ ናቸው፡፡
የግብጽ ወጥ ያልሆነ አቋም የፖለቲካ ሴራ እና ሰጥቶ የመቀበል መርህን የሚቃረን መሆኑን አስረድተዋል።
ግብጽና ተከታዮቿ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲስተጓጎል በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ለመግባት በጀት በመመደብ ጭምር ለትርምስ ለመዳረግ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ድርድሩ መፍትሄ ባያመጣም ግንባታውን በተገቢው በማስቀጠል ግድቡን ለመፈጸም የመላው ኢትዮጵያዊ ርብርብ እንደሚያስፈልግም ዶክተር ተመስገን አብራርተዋል።