ብርጋዴል ጄኔራል አከለ አሳዬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ - ኢዜአ አማርኛ
ብርጋዴል ጄኔራል አከለ አሳዬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2/2013 ( ኢዜአ) ብርጋዴል ጄኔራል አከለ አሳዬ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ብርጋዴል ጄኔራል አከለ አሳዬ ከአባታቸው ከአቶ አሳዬ አስፋውና ከእናታቸው ወይዘሮ ማሚት ትኩዬ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በ1961 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡
ብርጋዴል ጄኔራል አከለ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኢህዴን/ ደርግን ለመጣል ያካሄድ የነበረውን የትጥቅ ትግል ከተቀላቀሉበት ከ1978 አስከ 1984 ዓ.ም ከተራ ተዋጊነት እስከ ሬጅመንት ኮሚሳርነት በሚደርሱ ኃላፊነቶች ማገልገላቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል አከለ ከ1984 እስከ 2004 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት የኮማንዶና የአየር ወለድ ስልጠና ተከታትለዋል፡፡
በመቀጠልም በተጠቀሱት ዓመታት በዓለም አቀፍ ስምሪት የሩዋንዳ ሠላም አስከባሪ ሻምበል አዛዥ፣ የደብረ ዘይት ኮማንዶ ማሰልጠኛ አዛዥ፣ የ11ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ፣ የመከላከያ ዘመቻ መምሪያ፣ የ110ኛ ኮር እና የ31ኛ ከፍለ ጦር ትምህርትና አስተዳደር፣ የማዕከላዊ ዕዝ እና የመከላከያ ኢንዶክትሬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ማዕከል ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡
በመጨረሻም የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል ማደራጃና ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገራቸውንና ሕዝባቸውን በታታሪነትና በቅንነት ማገልገላቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር ኢንዶክትሬሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ብርጋዴል ጄኔራል አከለ አሳዬ በድልና በመስዋዕትነት የደመቀው የኢህዴን ሠራዊት ታሪክ እና ያልተንበረከኩት በሚል ርዕስ ሁለት መጽሃፍትን ለንባብ ማብቃታቸውም ተገልጿል፡፡
ሶስተኛ መጽሃፋቸውን ለማሳተም ዝግጅታቸውን አጠናቀው እንደነበረም በሕይወት ታሪካቸው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል አከለ አሳዬ ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ ባደረባቸው ሕመም በጦር ኃይሎችና በጳውሎስ ሆስፒታሎች በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ52 ዓመታቸው የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡