ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የመግባት ፍላጎት መቼም አይሳካም----በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን

መጋቢት 2/2013 /ኢዜአ/ አሜሪካ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለመግባት ያላቸው ፍላጎት አይሳካም ሲሉ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሰላማዊ ሰልፍ ድምጻቸውን አሰሙ።

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አለምአቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል እንዲገነዘብ በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል።

በዋሽንግተን ዲሲና በኒውዮርክ ግዛቶች በርካታ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ገጽ ለማጠልሸት በአለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን በህወሃት ደጋፊዎች የሚነዙ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በመቃወም ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ማንም አገር ጣልቃ የመግባት መብት እንደሌለው አሜሪካም ሆነች የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያሳዩትን አዝማሚ እንዲያስተካክሉ ጠይቀዋል።

ሰልፈኞቹ  ይዘዋቸው ከወጡ መፈክሮች ውስጥ 'በኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ዓመታት ለተፈጸመው ጥፋት ተጠያቂው የህወሃት ወንጀለኞች ቡድን ነው፣ ግድቡ የእኔ ነው፤ እንደጀመርነው እናጠቅቀዋለን፣ ስልጣን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንጂ፤ በጠመንጃና በአሸባሪነት መያዝ አብቅቷል፣ በትግራይ ህዝቡ ወደተለመደ ኑሮው እንዲመለስ መንግስት የጀመረውን ጥረት እንዲያጠናክር እንጠይቃለን' የሚሉት ይገኙበታል።

በኒውዮርክ የተደረገው ሰልፍ የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ያለስምምነት ያጠናቀቀውን ስብሰባ ተከትሎ በድጋሚ የሚያደርገው ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት አቋሙን እንዲያስተካከል የሚጠይቅ ነው።

በዋሽንግተንዲሲና በኒውዮርክ ከተሞች የተደረገውን ሰልፍ በርካቶች የደገፉት ሲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ''አሜሪካ የምትኖሩ ወገኖቻችን በጠንካራ የሃገር ፍቅር ስሜት፤ የኢትዮጵያን ትክክለኛ እና ወቅታዊ ገፅታ አስመልክቶ፤ ለሰፊው ዓለም እውነታውን ያስተጋባችሁበት ታሪካዊ ሰልፍ በእጅጉ የሚደነቅ ነው'' ብለዋል።

በተመሳሳይ በሌሎች ክፍለ ዓለማት በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ እውነት ለምዕራቡ ዓለም ለማስገንዘብ ዝግጅት ላደረጉት አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

''በቀጣይ ሁላችንም እናት አገራችን ኢትዮጵያን ከፊት አስቀድመን የፀና አንድነታችንን በማጥበቅ ወቅቱ ለሚጠይቀን ታሪካዊ ትግል በጋራ እንደምንረባረብ ከወዲሁ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ'' ብለዋል አቶ ደመቀ።

በተመሳሳይ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል።

ሰልፈኞቹ የህወሃት  ቡድን በሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመውን የአገር ክህደት  በማውገዝ   መንግስት የወሰደውን የህግ ማስከበር እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም