ቀጥታ፡

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ችግሮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት አገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2013 /ኢዜአ/ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት አገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ገለጸ።

በአዲስ አበባ፣ በሃዋሳ እና በባህርዳር የሳኒታይዘር ማምረቻ ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና ምርቱም ለአቅመ ደካሞች በነፃ የሚከፋፈል መሆኑን ገልጿል።

ሁለገብ የኪነጥበብ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ የሚመራው ዓለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት "ግሎባል አሊያንስ" የኢትዮጵያዊያንን መብት በማስከበር፤ ችግር ሲደርስባቸውም ከጎናቸው በመቆም የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል።

በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ዳያስፖራውን በማስተባበር ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱም ይታወቃል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ፈጣን ምላሽ በመስጠት አገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጿል።

ለአብነትም በጌዲዮና ጉጂ፣ በትግራይና በመተከል በተፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በመድረስ የተሰሩ ስራዎችን አንስቷል።

የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ግሎባል አሊያንስ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

በቅርቡም በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሳኒታይዘር ማምረቻ በማቋቋም ምርቱ ለአቅመ ደካሞች ይከፋፈላል ብሏል።

ታማኝ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገራት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ችግር ሲፈጠር ችግሩን የራሱ አድርጎ አፋጣኝ መፍትሄ መፈለግ እንዳለበትም አሳስቧል።

በታማኝ በየነ የሚመራው ግሎባል አሊያንስ በአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በአሜሪካ የተቋቋመ ሲሆን ላለፉት ሰባት ዓመታት ዳያስፖራውን በማስተባበር በኢትዮጵያ ለሚደርሱ ሰብዓዊ ቀውሶች ምላሽ እየሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም